ከማታምኚው ሰው ጋር በፍቅር መውደቅ ቀላል ነገር ነው ከእርሱ ጋር መኖር ግን ከባድ ነው።
ትክክለኛ እና ዘላቂ የሆኑ ግንኙነቶች የሚመሰረቱት በመተማመን ነው። መተማመን መሰረታዊ ነገር ነው ምክንያቱም ግንኙነታችሁ ማደግ እንዲችል አመቺ የሆነ አካባቢን ይፈጥራል። ግንኙነታችሁ ቀጣይነት እንዲኖረው የምታገቢውን ሰው ባለፈው፣ አሁን ባለው እና ወደፊት በሚገጥምሽ ነገር ሁሉ ልታምኚው ይገባል።
መተማመን ለመገንባት ጊዜ እና ጥረት የሚጠይቅ፤ በቀላሉ ሊጠፋ የሚችል እንዲሁም ለመመለስ በጣም አዳጋች የሆነ ነገር ነው። ነገር ግን ልትጠብቁት እና ልትንከባከቡት ከወሰናችሁ እንዲኖራችሁ የምታልሙትን ህይወት ሊሰጣችሁ የሚችል ትልቅ ነገር ነው።
ትክክለኛ ማንነትሽን ግለጪ
መተማመን ትክክለኛ ማንነትሽን መግለጥ እንድትችይ ያደርግሻል። በመጀመሪያ የግንኙነት ወቅቶች ሌላውን ወገን ለመመሰጥ የምናደርጋቸው ድርጊቶች እንዳሉ ሆነው መቀራረብ ግን ሊመሰረት የሚችለው በማወቅ እና በመታወቅ ላይ ነው። የፍቅር ጓደኛሽ ትክክለኛ ማንነትሽን ማወቅ አለበት። ሲደክምሽ፣ ስትናደጂ፣ ስትበሳጪ፣ ስትደሰቺ፣ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ስትሆኚ ምን ዓይነት ባህሪ እንዳለሽ ማወቅ አለበት። እርሱ በሚፈልገው ማንነት ሳይሆን በትክክለኛ ማንነትሽ ሊያፈቅርሽ ይገባል። ከዚህ የተለየ ከሆነ ዘላቂ አይሆንም።
በትክክለኛ ማንነትሽ መፈቀርሽን ማወቅሽ ዘና እንድትዪ እና እንዳትጨናነቂ ያደርግሻል። ተቀባይነትን አጣለሁ ብለሽ ሳትፈሪ ሀቀኛ እንድትሆኚ እና ጥሩ ስሜት እንዲሰማሽ ያደርጋል። ሰዎች በትክክለኛ ማንነታችን እንደወደዱን ማወቃችን አስደሳች እና የአዕምሮ እረፍት የሚሰጥ ነገር ነው። በማንነትሽ የወደደሽን ሰው አላስፈላጊ ጥረት በማድረግ የአንቺ ለማድረግ መልፋት አይጠበቅብሽም።
ግልፅ ውይይት
መተማመን ለግልፅ ውይይት በር ከፋች ነው። ፍቅረኛሽ በሆነ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚያስብ እና ምን ሊያደርግ እንደሚችል ማወቅ የማትችዪ ከሆነ እና ይህም የሚያስጨንቅሽ ከሆነ ግልፅ ውይይት ማድረግ ከባድ ነው። ውይይት ትኩረት ማድረግን የሚጠይቅ ነው።
ለውጤታማ ውይይት አምስት መሰረታዊ ነገሮች፡
- መጠየቅ፡ ሰዎችን እንደምታውቂ ግምት አትውሰጂ። አንዴ የተወሰኑ ጥያቄዎችን ከጠየቅሽ ማንነታቸውን ማወቅ ከባድ አይሆንም።
- ማዳመጥ፡ የተሻለ ተናጋሪ ለመሆን ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን አለብሽ (እሱ ሲናገር ምላስሽን አታዘጋጂ፤ አዳምጪ)። በዚህ ጊዜ የተናጋሪውን ምልከታ በተሻለ መረዳት ትችያለሽ።
- መመልከት፡ ያገኘሽውን መረጃዎች ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ሞክሪ።
- ምን እያሰብሽ እንደሆነ ሌሎች እንዲያውቁ አድርጊ፡ የምታስቢውን ተናገሪ። ስለራስሽ እውነቱን መናገር ሌላው ሰው አንቺን እንዲያውቅ እና እንዲረዳሽ ያደርጋል።
- ፍቅር እልፍ ሀጥያትን እንደሚሸፍን አስታውሺ፡ ሰዎችን መረዳት እና በማንነታቸው የመቀበል አላማ ካለሽ ውይይት ማድረግ ቀላል ነው። ነገር ግን የአንቺ መንገድ ብቻ ቅዱሱ መንገድ እንደሆነ ልታሳምኛቸው ከሆነ ፍላጎትሽ ይህ ውይይት አይባልም። እናም ይህ ፍቅር አይደለም።
ፍትሀዊ ግጭቶች
ውይይት ማድረግ ከቻላችሁ ፍቅረኛሽን ማመንሽ ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ ፍትሀዊ እንድትሆኚ ይረዳሻል። ማወቅ ያለብሽ ነገር ህይወት ካለው እና ከሚተነፍስ ሰው ጋር እየኖርሽ መጋጨታችሁ የማይቀር ነገር ነው። ግጭታችሁ የሚሰብራችሁ ይሁን ወይም ግጭቱን ፈታችሁ የበለጠ በመቀራረብ ወደፊት መሄዳችሁ የሚወሰነው ግጭቱ ፍትሀዊ በመሆኑ ላይ ነው። ፍትሀዊ ግጭት ምንድነው? አብዛኛው ሊቅ ፍትሀዊ ግጭት የሚከተለውን ያካትታል ብለው ይስማማሉ፡
- በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ማተኮር፡ ያለፈን ስህተት ለመምዘዝ አሁን ጊዜው አይደለም። አሁን ላይ የተፈጠረው ነገር ላይ ብቻ ትኩረት አድርጊ።
- በማይመጥን ስም መጠራራትን እና መሳደብን እንቢ ማለት፡ ማወቅ ያለብሽ የውይይቱ አላማ ግጭትን መፍታት እንጂ ሌላኛውን ሰው በመሰባበር የአንቺን ድል ማወጅ አይደለም። የፍቅር ጓደኛሽ ካላከበረሽ ወይም እያጠቃሽው እንዳለ ከተሰማው አንቺን ማዳመጥ ያቆማል።
- አጠቃላይ ከሆነ ንግግር ይልቅ በተፈጠረው ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግ፡ “አንተ ሁሌም” ወይም “አንተ መቼም” የሚሉ ቃላት እውነታውን የሚያንፀባርቁ እና የፍቅር ጓደኛሽ እራሱን በመከላከል ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርግ የሚያደርጉ ናቸው። የተፈጠረውን ነገር ላይ እና የተፈጠረው ነገር በእናንተ ውስጥ በፈጠረው ስሜት ላይ ብቻ ትኩረት አድርጊ።
መተማመንን መገንባት
መተማመን በሁለት ሰዎች መሀል ዝም ብሎ አይፈጠርም፤ የሚዋደዱ ቢሆንም እንኳን። በእውነት ፍቅረኛሽን የምትወጂውና የተሻለ ነገር የምትመኚለት ከሆነ ልትታገሺው ይገባል። ስራ ይፈልጋል። እምነትን መገንባት ጊዜ ይፈልጋል፤ ፍቅረኛሽን ልትታመኚ የሚገባሽ መሆኑን እና እሱንም ልታምኚው የምትችይ መሆንሽን ልታሳዪ ይገባል። የፍቅር ጓደኛሽ የማመን ችግር ካለበት እምነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የተለያዩ ነገሮችን መፍጠር ትችያለሽ። ፍቅረኛሽን አዳምጪ፣ እሱን እና ሀሳቡን አክብሪ እንዲሁም በማንነቱ ተቀበይው። ያለፈ ታሪክሽን ንገሪው። አንቺ እንደምታምኚው ስታሳዪ እርሱም እንዲያምንሽ ይረዳዋል። አንቺ ግልፅ ሆነሽ ከቀረብሽው እሱም ግልፅ መሆን እንደሚችል እንዲያስብ ያደርገዋል።
ልታምኚው እንደማትችዪ ከምታስቢው ሰው ጋር ግንኙነት ውስጥ ካለሽ ችላ አትበይ። ከዚህ ቀደም ከተጎዳሽ ሌላን ሰው ማመን እጅግ ከባድ ሊሆን ይችላል። ያለፈው ታሪክሽ የማመን አቅምሽን ሊገድብ አይገባም። ሰውን ለማመን የምትቸገሪ ከሆነ ሌላውን በማመን ከሚገኝ መልካም ግንኙነት እንዳትጎጂ የምክር አገልግሎት ልታገኚ ይገባል። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሰውን ማመን የማትቸገሪ ከሆነ እና አሁን ግን ከዚህ ሰው ራስሽን እንድትጠብቂ ውስጥሽ እየነገረሽ ከሆነ እንደማስጠንቀቂያ ውሰጂው። ስለዚህ ሰው ማንነት፣ ከሌሎች ጋር ስላለው ግንኙነት እና በአንቺ ላይ ስላለው እምነት በሚገባ አጥኚ። ምን አልባት ውስጥሽ ጥሩ መረጃ እየሰጠሽ ይሆናል።
ፍቅረኛሽን ማመን ከብዶሻል? እንግዲያውስ ብቻሽን እንዳልሆንሽ እወቂ። እና ስለምታልፊበት ነገር የምታወሪው ሰው ቢኖር በእውነት ይረዳል። ሚስጥርዎ የተጠበቀ እና ሁልጊዜም በነፃ የሚሰጥ አገልግሎት ነው።