ምናልባት ችግር እንዳለብህ ላታውቅ ትችላለህ። ሁሉም ጓደኞችህ ልክ እንዳንተ ስልኮቻቸው ላይ ተጠምደዋል። የምታውቃቸው ሰዎች ሁሉ በየደቂቃው የinstagram እና የfacebook ገፃቸውን ያያሉ። በየቀኑ በየሰአቱ youtube እና Tiktok በማየት ያሳልፋሉ። አንተም እንደ እነሱ ነህ።
ምን ያህል ሰአት ኢንተርኔት ላይ ማሳለፍህ አይደለም ችግሩ። ችግሩ ኢንተርኔት ላይ የምታጠፋው ሰአት ምን ያህል አንተ እና ህይወትህ ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር አለማወቅህ ነው።
ይሄ ፀረ ቴክኖሎጂ ወይም ፀረ ማህበራዊ ሚዲያ መሆን አይደለም። ነገር ግን ከኢንተርኔት ጋር የተገናኙ ነገሮች በግድ በሰው ህይወት ጣልቃ መግባት ሲጀምሩ እንዲሁም በቤተሰብ፣ በጓደኞች እና በስራ ቦታ አካባቢ ከባድ ጭንቀት ሲፈጥሩ ማየት ሊያሳስብህ የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ ነው።
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት በዶ/ር ኪምበርሊ ያንግ የኢንተርኔት ሱስ እንዳለብን እና እንደሌለብን ለማወቅ የተዘጋጁ መጠይቆች ናቸው። ከ 8ቱ ጥያቄዎች ለ5ቱ መልስዎ “አዎ” ከሆነ የዲጂታል ሱስ አለብህ ማለት ነው።
- በኢንተርኔት እንደተጠመድክ ይሰማሃል? (ስለ ቀድሞ የኢንተርኔት እንቅስቃሴ እያሰብክ ወይም ቀጣዩን ኢንተርኔት ላይ ምታደርገውን ጊዜ እየጠበቅክ ነው?)
- እርካታን ለማግኘት ኢንተርኔት በብዛት መጠቀም አለብኝ ብለህ ታስባለህ?
- የኢንተርኔት አጠቃቀምህን ለመቆጣጠር፣ ለመቀነስ ወይም ለማቆም በተደጋጋሚ ያልተሳካ ጥረት አድርገሃል?
- የኢንተርኔት አጠቃቀምህን ለማቆም ወይም ለመቀነስ በምትሞክርበት ጊዜ እረፍት ማጣት፣ ስሜታዊነት፣ ድብርት ወይም ብስጭት ይሰማሃል?
- መጀመሪያ ካቀድከው ጊዜ በላይ ኢንተርኔት ላይ ብዙ ጊዜ ታሳልፋለህ?
- በኢንተርኔት ምክንያት አስፈላጊ የሆነ ግንኙነትን፣ ስራን ወይም የትምህርት እድልን ለአደጋ አጋልጠህ ታውቃለህ?
- ምን ያህል ጊዜ ኢንተርኔት ላይ እንደምታጠፋ ለመደበቅ ስትል ቤተሰቦችህን፣ ጓደኞችህን ወይም ሌሎች ሰዎችን ዋሽተህ ታውቃለህ?
- ከችግሮች ለማምለጥ ወይም እንደ አቅመ ቢስነት፣ የጥፋተኝነት ስሜት፣ ጭንቀት ወይም ድብርት የመሳሰሉ አሉታዊ ስሜቶችን ለመገላገል ኢንተርኔት ትጠቀማለህ?
እነዚህም ጥያቄዎች ከመለስክና የኢንተርኔት ሱስ እንዳለብህ ከተረዳህ ከዚህ ለመውጣት ምን ማድረግ እንዳለብህ ትጠይቅ ይሆናል።
ተስፋ አትቁረጥ ይህን ሱስ ማሸነፍ ትችላለህ
አሁንም ራስን ወይም ሌሎችን አይጎዳም ብለህ በማሰብ የኢንተርኔ አጠቃቀምህን የመቀነስ ሐሳብህን እያመነታህ ከሆነ ለአንተም ሆነ ለግንኙነትህ ጎጂ ሊሆን ይችላል።
ውጤቶች እንደሚያሳዩት የኢንተርኔት /የስክሪን/ ሱስ አእምሮን ሊጎዳ ይችላል። ከመጠን በላይ መነቃቃት የአንጎልን መዋቅርና ተግባር ሊጎዳ ይችላል። በተለይ የሰው አዕምሮ ሙሉ በሙሉ ካልዳበረ (እስከ ሃያዎቹ አጋማሽ ድረስ) ተጽዕኖዎቹ ሰፊ ናቸው። ለምሳሌ
- መበሳጨት
- ለመተኛት መቸገር እንቅልፍ ማጣት
- ትኩረት ማድረግ አለመቻል
- ስሜቶቻችንን እና ምላሾችን መቆጣጠር አለመቻል
- ለሰዎች ርህራሄ የማሳየት ችሎታ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል
- ከአደንዛዥ ዕጽ ፍላጎት ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ፍላጎቶችን ሊያስከትል ይችላል
- በትንንሽ ነገሮች መጨነቅ እና ውጥረትን ይፈጥራል
የስክሪን ሱስ ተጨማሪ ችግሮች
እውነተኛ የሆኑ ግንኙነቶችን ይጎዳል፦ በማህበራዊ ሚድያ ሱስ ምክንያት ውጫዊ የሆነው የኢንተርኔት ግንኙነት የእውነተኛ ግንኙነቶችን ቦታ መውሰድ ይጀምራል።
ኃላፊነት የጎደለው ሰው መሆን፦ ሳታስተውለው ራስህን ለሰአታት ስልክህ ላይ አፍጥጠህ ጊዜህን እያባከንክ ልታገኘው ትችላለህ። ምናልባት ይሄ ጊዜ የምታጠናበት፣ የምትተኛበት ወይም ቤትህ ውስጥ አንዳንድ ስራዎችን የምትሰራበት ጊዜ ሊሆን ይችል ነበር።
እንዲሁም በስራ ቦታህ ላይ ሁልጊዜ ማህበራዊ ሚዲያን ለመጠቀም ስልክህን የምታነሳ ከሆነ ምርታማነትን በመቀነስ በሙያህ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።
ከእውነተኛ የህይወት ክስተቶች ያጎድላል፦ ብዙ ጊዜ ኢንተርኔት ላይ ማሳለፍ በዙሪያህ ያለውን የእውነተኛ ህይወት ክስተቶች ችላ እንድትል ያደርግሃል። ቤተሰቦችህ፣ ባለቤትህ ወይም ልጆችህ ሊያናግሩህ ፈልገው ነበር አንተ ግን ስልክህን አስበልጠህ አልመለስክላቸውም። ጓደኛህ ሊያገኝህ ፈልጎ ነበር አንተ ግን ስልክህ ላይ ለመቆየት ብለህ እንደማትችል ነግረኸዋል።
ውስጥህ እንዲያዝ ያደርጋል፦ ስልክህን መተው ስላልቻልክ ከስልክህ ውጪ ያለውን እውነተኛ ህይወት ረስተኸዋል።
መሰልቸት፦ ስልክህን እየተጠቀምክ ካልሆነ ህይወት በጣም አሰልቺ እንደሆነች ታስባለህ። በህይወትህ ውስጥ እንዴት በቀላሉ ደስታን መፍጠር እንደምትችል አታውቅም።
እንዚህ ነገሮች በአንተ ላይ መሆን የለባቸውም። ዛሬ ጤናማ የሆነ የኢንተርኔት አጠቃቀምን መጀመር ትችላለህ።
ጤናማ የኢንተርኔት አጠቃቀም ዘዴን እንደ ጤናማ የአመጋገብ ስርአት ማየት ትችላለህ። ጤናማ ሆኖ ለመቆየት ጤናማ የሆኑ ምርጫዎችን መምረጥ ያለብህ ጊዜ ይኖራል። ጤናማ የኢንተርኔት አጠቃቀም ኢንተርኔት ላይ ምን እየሰራህ እንደሆነ እና ምን ያህል ሰአት እየተጠቀምክ እንደሆነ ማስተዋልን ያካትታል። በተጨማሪም አጠቃቀምህን በማስተካከል ለስራ፣ ለትምህርት እና ለመዝናናት መጠንህን ሳታልፍ መጠቀም መቻል ነው።
እንነዚህን አምስት ነገሮች ሞክር
በቀን ውስጥ ስልክህን የማትጠቀምበት ሰአት ይኑርህ፦ ለምሳሌ ምግብ በምትመገብበት ጊዜ ስልክህን አርቀህ አስቀምጥ ወይም ከምሽቱ 4 ሰአት በኋላ ስልክህን ላለመጠቀም ለራስህ ገደብ አድርግ ወይም በቀን ውስጥ ከትምህርት ወይም ከስራ በኋላ ለሁለት ሰአታት ስልክህን አስቀምጠህ እረፍት ውሰድ። ለአንተ የሚመቸውን ጤናማ የኢንተርኔት አጠቃቀም መርጠህ እሱን ተከተል። የተወሰነ ጉልበት ሊጠይቅ ይችላል። ነገር ግን ውሎ አድሮ የበለጠ ደስታን ያመጣል።
በምትተኛበት ጊዜ ስልክህን አርቀህ አስቀምጥ፦ ጠዋት ላይ ከእንቅልፍህ እንደተነሳህ መጀመርያ የምታየው እንዲሁም ማታ ከመተኛትህ በፊት የምታየው ስልክህን ነው? ለአእምሮህ እና ለአይንህ እረፍት ልትሰጠው ይገባል። ስልክህ አጠገብህ ከሆነ ልትቸገር ስለምትችል በምትተኛበት ጊዜ ካንተ አርቀህ ማስቀመጥ አለብህ።
ስልክህ ላይ ያሉ ማሳወቂያዎችን ቀንስ፦ ስልክህ ላይ ያሉ ማሳወቂያዎች በሙሉ ከበሩ ስልክህ መጮሁን አያቆምም። እስቲ ራስህን ጠይቅ አንድ ሰው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ፖስት ባደረገ ወይም ፎቶዎች ላይክ ባደረገ ቁጥር ወይም ኢሜይል በደረሰህ ቁጥር ማየት አለብህ? አንዳንድ ማሳወቂያዎችን እንዳይረብሹህ ማጥፋት ትችላለህ።
የምታያቸውን ተከታታይ ፊልሞች ወይም ቪዲዮዎች ቁጥር ቀንስ፦ ቪዲዮዎችን ወይም ተከታታይ ፊልሞችን ከመጠን በላይ የማየት ዝንባሌ ካለህ ልክ የምግብ አወሳሰድህን እንደምትገድብ ለራስህ ገደብ አዘጋጅ።
የማህበራዊ ሚዲያ እረፍት ውሰድ፦ በምን ያህል ጊዜ የ facebook ገጽህን ትምለከታለህ? የተቀየረ ነገር እንዳለ ለማረጋገጥ ስንት ጊዜ የfacebook app እንደከፈትክ ቆጥረህ ታውቃለህ? እመነኝ እረፍት ብትወስድ አይጎዳህም። ለአንድ ሳምንት ያህል ማህበራዊ ሚዲያን መጠቀም ብታቆም ምን ያህል ተጨማሪ ጊዜ እንዳለህ ማወቅ ትችላለህ። ማህበራዊ ሚዲያን መቀነስ ከእያንዳንዱ ፖስት ጋር ለመራመድ በመሞከር የሚፈጠረውን ጭንቀት ይቀንሳል።
ስኬታማ የሆነ ጤናማ የኢንተርኔት አጠቃቀምን ለመጀመር ተጠያቂነት ዋናው ነገር ነው። ድጋፍ የሚያስፈልግዎት ከሆነ፤ ከእኛ ቡድን መሀል አንድ ሰው ይሄን መንገድ አብሮት መሄድ ይፈልጋል። የትኛውም አይነት ሱስ ቢኖርቦት ብቻዎን አይደሉም። መረጃዎትን ከስር ይተዉልን እና ከእኛ ቡድን መሀል በቅርቡ አንድ ሰው ያናግሮታል።