ሞት እስከሚለየን ድረስ

ከባለቤቴ ጋር ሁልጊዜ ስለሞት ስናውራ “ከአንቺ በፊት እኔን” ይለኝ ነበር። ይህን የሚለው ከፍቅሩ የተነሳ እንደሆነ ባውቅም አላምነውም ነበር። እንዳላምነው ያደረገኝ ምናልባትም የአብዛኞቹ ቤተሰቦቹ እድሜ ከዘጠና መብለጡ ይመስለኛል። የእኔ ደግሞ የእርሱ ተቃራኒ ነበር። ለዛም ነው ከባላቤቴ ቀድሜ መሞቴን እርግጠኛ ከመሆን ባለፈ፤ ባሌ ቀብሬ ላይ እንዴት ማልቀስ እንዳለበት በቀልድ አስመስዬ የምነግረው። ሁሉም ሰው ትርጉም ያለው ህይወት እንደኖርኩ፤ ግርምሽን እንዳጎደልኩት፤ በቤቴ እንደምናፈቅ እንዲያውቅ ስለምፈልግ ቀብሬ እንዲደምቅ እየሳቅሁ አስጠነቅቀው ነበር። “ሰምተኸኛል አይደል ግርምሽ እሪሪ. . .ማለት አለብህ! ለያዥ ለገናዥ ማስቸገር! አፈር ነው የለ ጭቃ ነው የለ በቃ መንደባለል። እሺ ግርምሽ! ሰማኸኝ አይደል?” ይስቅብኛል፤ “ሚቀድመውን ማን ያውቃል ብለሽ ነው?” ይለኝ ነበር። እያሾፈብኝ ይመስለኝ ነበር። በዛ ላይ በዙሪያችን ያሉ ያላገቡ ሴቶች መኖራቸውን ሳስብ በየትኛዋ ይተካኝ ይሆን የሚለው ሃሳብ እጅግ ይረብሸኝ ነበር። እንዳሰብኩት ግን አልሆነም ግርምሽ ታማኝ ነበር። እንደቃሉ አደረገው። እግዚአብሔርም የአፉን ቆጥሮ ከእኔ ቀድሞ ወሰደው። ግርምሽ ጥሎኝ ሄደ።

ምንም እንኳን በትዳር ለአስራ ሰባት አመት አብረን ብንኖርም ፍቅራችን ግን ልክ እንደ አዲስ ፍቅረኞች ነበር። አልተሰለቻቸንም ነበር። ከስራ ሰአት ውጪ ያለውን ጊዜ ሁሌም አብረን ነበር ምናሳልፈው። አንዲት ቀን ግን የህይወታችንን ምዕራፍ ላይመለስ ቀይራው አለፈች። ግርምሽ አልፎ አልፎ የሚሰማው ያልተለመደ አይነት የህመም ስሜት ቢኖርም፤ ትንሽ ሲቆይ ይተወኛል በሚል ምክንያት ወደ ህክምና ቦታ አልሄደም ነበር። አንድ ቀን ግን ህመሙ ትንሽ ጠንከር ሲልበት ምንም እንኳን እሱ ደህና ነኝ ቢልም፤ መሄድ አለብን ብዬ በግድ ሆስፒታል ሄድን። ሄደን የሰማነው የህክምና ውጤት ግን ጭራሽ ያልጠበቅነው ጀሮ ጭው የሚያደረግ ነበር። የህመሙ ምክንያት የአንጀት ካንሰር እንደሆነ እና ያለበትም ሁኔታ አራተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ሃኪሞቹ ነገሩን። ይህም በሽታው መዳን ከማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱንና በዚህም ሁኔታ ብዙ በህይወት መቆየት እንደማይችል ነገሩን። ድንጋጤውና ሀዘኑ መግለጥ ከምችለው በላይ ነበር። እኔም ሃኪሞቹ በነገሩንና በተለያዩ መንገዶች ካነበብኳቸው መረጃዎች በመነሳት ግርምሽ በህይወት ለመኖር ያለው ጊዜ በጣም ጥቂት መስሎ ስለተሰማኝ፤ ከስራ እረፍት ወስጄ ሙሉ ጊዜዬን ከእርሱ ጋር ለማሳለፍ ወሰንኩ።

የካንሰር ስርጭቱ ከቁጥጥር ውጪ ቢሆንም የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ወስነን ግርምሽ ህክምናውን ጀመረ። ለዘጠኝ ተከታታይ ወራትም ህክምናውን ወሰደ። በዚህም ወቅት አራት ዋና ዋና ቀዶ ጥገናዎችን እና ብዙ መለስተኛ የተመላላሽ ሕክምናዎችን አድርጓል። በወቅቱ ኬሞቴራፒ በሰውነቱ ውስጥ ያለማቋረጥ እንዲሰራጭ የሚያስችል ቀጭን ቱቦ ተገጥሞለት ነበር። በሰውነቱ ውስጥ ያለው የፈሳሽ መጠን በጣም እንዳይወርድና ድንገተኛ የኩላሊት ስራ ማቆም እንዳይከሰት በደም ስር ውስጥ ፈሳሽ እንዴት መስጠት እንዳለብኝ ተምሬ ነበር። ይህንንም ማድረግ ጭንቀቱ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች በአግባቡ ካልተሰጡና በቂ ካልሆኑ ከቀዶ ጥገናው ጋር ተዳምሮ የደም መርጋት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል። ስለዚህ የደም መርጋት ወደ ሳምባው ወይም ወደ ልቡ የሚሄደውን መስመር እንዳይዘጋ ለመከላከል በየቀኑ በሆድ በኩል የሚሰጥ የደም ማቅጠኛ መድሀኒት በመርፌ እሰጠው ነበር። ይህም ከባድ ጭንቀት ፈጥሮብኝ ነበር። እንደውም የሆነ ጊዜ ላይ ሁሉም ነገር ከአቅሜ በላይ እንደሆነብኝና በዚህ መልኩ መቀጠል እንደማልችል ለልብ ጓደኛዬ ነግሬያት ነበር። ይሁንና ለባለቤቴ ካለኝ ፍቅር የተነሳ እንዲሁም በቤተሰቦቼና ጓደኞቼ ድጋፍ ጠንክሬ ማስታመሜን ቀጠልኩ።

ህክምናው ከተጀመረ ከዘጠኝ ወራት በኋላ የመጨረሻው ቀዶ ጥገና ተደረገለት። እናም ካንሰሩ አንጀቱን ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጪ እንዳደረገውና ከዚህ በኋላ ምንም ማድርግ ስለማይቻል ወደ እቤት እንድንወስደው እንዲሁም ቀጥሎ ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ሁኔታዎች እና ማድረግ ስላለብን ነገር በዝርዝር ተነገረን። ወደ ቤት ከተመለሰ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ህመሙ በጣም ኃይለኛ ሆነ። ማስታገሻ መድሃኒት በየሰዓቱ ነበር የሚወስደው። ብዙም ሳይቆይ ራሱን መሳትና መቃዠት ጀመረ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከአንድ ሳምንት በላይ ቆይቷል። ከዚያም አንድ ቀን፣ በአርባ ስምንት ዓመቱ፣ የካንሰር ምርመራ ከተደረገ ከአስር ወራት በኋላ፣ እጁን እንደያዝኩ፣ አንገቱን ወደ እኔ አዞረ እና በትጋት ለመጨረሻ ጊዜ “እወድሻለሁ” አለኝ። ከዚያም ሶስት ጊዜ ጠቀሰኝ፣ ይህም ሁል ጊዜ ሁሉም ነገር ደህና እንደሚሆን የሚያረጋግጥልኝ መንገድ ነበር። ለመጨረሻ ጊዜ እየተሰናበተኝ እንደሆነ ገባኝ። ያን ምሽት በእጆቼ እንዳቀፍኩት የመጨረሻውን ትንፋሽ ተነፈሰ። በዚያች ቀን አርሱን በማጣት ያየሁት መከራ አንድ ብሎ ተጀመረ።

ብዙ ነገሮች ይናፍቁኛል ብዙ ጊዜ ከስራ ስመለስ የግርምሽ ጠንካራ ክንዶች ውስጥ ተወሽቄ ጭንቀቶቼን ሁሉ ብረሳቸው ብዬ እመኛለው። የሚጠብቀኝ ግን የቀዘቀዘ ባዶ ቤት ብቻ ነው።

አሁን ላይ ግርምሽ ካለፈ ሶስት አመት ሆኖታል ሃዘኑ ግን ልክ ትናንት እንዳጣሁት አይነት ነው ሚሰማኝ። ብዙ ጊዜም ራሴን በመሪር ሀዘን ውስጥ አገኘዋለው። ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ፤ ያለ ግርምሽ መኖር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በአርባ አምስት አመቴ በሚገባ ተምሬያለሁ። ብዙ ነገሮች ይናፍቁኛል ብዙ ጊዜ ከስራ ስመለስ የግርምሽ ጠንካራ ክንዶች ውስጥ ተወሽቄ ጭንቀቶቼን ሁሉ ብረሳቸው ብዬ እመኛለው። የሚጠብቀኝ ግን የቀዘቀዘ ባዶ ቤት ብቻ ነው። ድሮ አብረን ምናውቀውን የጋራ ወዳጃቸንን መንገድ ላይ አጊኝቼው፤ እገሌን አገኘሁት፤ ወፍሯል፤ አርጅቷል ብዬ ለእርሱ መንገር ይናፍቀኛል። ቀልድ ስሰማ ነግሬው አብረን መሳቅ ያምረኛል። ለተለያዩ ዝግጅቶች የጥሪ ወረቀት ሲደርሰኝ በፊት ላይ ከነ ባለቤትዎ ተብሎ ይፃፍበት የነበረውን ቦታ ትኩር ብዬ አየዋለው፤ አሁን ላይ ባዶ ነው። ጥልቅ ባዶነት ይሰማኛል፤ ቦታው ላይ ስሆንም በብዙ ግርግር መሃል እንኳን ብቻዬን እንደሆንኩ ይሰማኛል። ትላንት ወደፊት ብለን ያቀድናቸውን ጊዜያት ዛሬ ላይ ለብቻ ሆኖ ማሰብ፤ እንጎበኛቸዋለን ብለን ያሰብናቸው ቦታዎች ብዛታቸው፤ አንዱም ሳይሆን ሲቀር፤ ይባስ ብሎ ያሉበትንም መጥላት፤ ብቻ በጣም ከባድ ነው።

በአስራ አንድ አመቷ ያጣናትን ልጃችንን እንዳልረሳትና አሁንም እንደሚወዳት ሊነግረኝ ሲፈልግ፤ ትንሽዬ ቢጫ አበባ ይዞልኝ ይመጣ ነበር። እንዳይረብሸኝ ስለሚሰጋ ቃል አያወጣም ነበር። ቢጫ አበባ በጣም ትወድ ነበር። ሁልጊዜ ለእርሱዋ ያረግ እንደነበረው አበባውን ሰጥቶ ያቅፈኝ ነበር። አሁን ስሜቴንም ሀዘኔንም ሚጋራኝ የለም። የተሰበረ ልቤን ይዜ ብቻዬን ዝም።

በአጭሩ ለመናገር፣ የሚወዱትን ማጣት ከባድ እንደሆነ አይቻለው። ግን ደግሞ፣ ተስፋ ቢስ መሆን እንደሌለብኝ እየተማርኩ ነው። በተመሳሳይ የህይወት መስመር እያለፉ ከሆነ በመንገድዎ የተማሩትን ወይም እየተቸገሩበት ያለውን ጉዳይ ለማካፈል የሚፈልጉ ከሆነ አድራሻዎን ያስቀምጡልን እና ከቡድናችን አንድ ሰው በቅርቡ ያገኝዎታል።

ፎቶ በ: Martin

ይህንን ብቻውን መጋፈጥ የለብዎትም ፡፡ ከአማካሪ ጋር ይነጋገሩ ፣ ሚስጥራዊ ነው ፡፡


እኛ ከእርስዎ ጋር መገናኘት እንድንችል እባክዎ ከዚህ በታች ያለውን ቅጽ ይሙሉ ፡፡ ካልተገለጸ በስተቀር ሁሉም መስኮች ያስፈልጋሉ ፡፡

የእርስዎ ፆታ:
የዕድሜ ክልል:

ተገቢውን አማካሪ እንዲመድብዎት የእርስዎ ፆታ እና ዕድሜ እንጠይቃለን። የአገልግሎት ውሎች & የግል መረጃ ደህንነት ፖሊሲ.

እነዚህ ጉዳዮች ለመቋቋም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ እራስዎን ወይም ሌሎችን ለመጉዳት እያሰቡ ከሆነ ፣ እባክዎን ይህንን ያንብቡ!