በስራዬ ደስተኛ አይደለሁም

ለአስራ ሁለት አመታት በጣም አስቸጋሪ በሆነ የስራ ሁኔታ ውስጥ አሳልፌለሁ። ወደ ስራ በገባሁኝ ቁጥር ከስራው ልባረር ወይም ልቀጥል እስካማላውቅ ድረስ የሚያስጨንቅ ነበር። የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ስላሉብኝ የግድ መስራት አለብኝ። የልጆች ት/ቤት፣ የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት ውጪ፣ አስቤዛ እና የመሳሰሉት። ባለቤቴም በህመም ምክንያት ገቢ ስለሌለው የቤቱን ወጪ በሙሉ የመሽፈን ሀላፊነት ያለብኝ እኔ ስለሆንኩኝ ስራዬን ማጣት የለብኝም። ስራው ለእኔም ሆነ ለቤተሰቤ ህልውና ወሳኝ ነው።

ጊዜው የተለያዩ ድርጅቶች በኢኮኖሚ ግሽበት ምክንያት ከስራ እየወጡ ያለበት ወቅት ነበር። እኔ ስራ በምጀምርበት ወቅት የምሰራበት ድርጅት ገቢ የከፋ የሚባል አልነበርም። በአንድ ቆንጆ ህንፃ አንዱ ወለል ሙሉ የእኛ ቢሮ ነበር። በቂ የስራ ስልጠና አልተሰጠኝም ሌሎች የስራ ባልደረቦቼን እንዳልጠይቅ የእነርሱም የስራ ጫና ከፍተኛ ነበር። እንደ እድል ሆኖ የቅርብ አለቃዬ ጋር ተግባባን። እኔ ያለሁበት የስራ ሀላፊነት ቀድሞ እሷ ትሰራው የነበረ በመሆኑ እንዴት መስራት እንዳለብኝ በደንብ አሳየችኝ። እግዚአብሔር ይስጣት ስራንዬ በአግባቡ በመወጣቴ ቀድሞ ከነበረኝ የስራ ሀላፊነት ከፍ ተደረኩኝ። የራሴ ቢሮም ተሰጠኝ።

ጫናው እየባሰ መጣ

የድርጅታችን እናት ድርጅት የእኛ ድርጅት የተከራየበት ህንፃ የኪራይ ወጪ ድርጅቱ ከሚያስገባው ገቢ ጋር የማይመጣጠን ነው በማለት ያለንበትን ቢሮ እንድንቀይር አስገደደን። ከዛም ያ ቆንጆ ቢሮ ወደ አንድ ትንሽዬ ቢሮ ተቀየረ። ከዋና ሃላፊያችን ውጪ ሁላችንም ከአንድ ጠረጴዛ እና ወንበር ውጪ የእኔ የምንለው ቢሮ አልነበረንም። በጣም ነበር የምንረባበሸው። የምንሰራው እና የምናወራው ሁሉ ለሁሉም ይታያል ይሰማል። የድርጅታችን አዲስዋ አለቃ ቢሮ እዛው አጠገባችን በመሆኑ የምትፈልገውን ሰው ስትጠራ እዛው ተቀምጣ በመሆኑ ትረብሸናለች። የምታወራው፣ የምታስበው እና የምትቆጣው ጮክ ብላ በመሆኑ የስራ ቦታውን ድባብ አጥፍታለች። ይህ ደግሞ እኔን በተደጋጋሚ ከስራዬ ያቋርጠኛል እና ሀሳቤን ሰብስቤ እንዳልሰራ ያደርገኛል። አዲስዋ ሀላፊ በምን እንደጠላችኝ ባላውቅም እኔ እንደ እሷ ታታሪ እንዳልሆኩኝ ለማሳየት የማይመለከተኝን ሁሉ ስለምታዘኝ ስራ በላዬ ላይ ተከምሮ ነበር። እናት ድርጅታችን ከእኛ ድርጀት የምትጠብቀው ነገር እየጨመረ በመጣ ቁጥር የእኛ ድርጅት ጫናው እየባሰ መጣ። የደንበኞቻችን የገንዘብ አቅም ውስን መሆኑን እናውቅ ስለነበር ፍላጎታቸው ማሟላት አልቻልንም ነበር። የእናት ድርጅታችን የስራ ቦታ ሌላ አካባቢ ስለሆነ የእኛን ደንበኞች ሁኔታ አላገናዘቡም እና የእኛን ግብ አሳካን አላሳካን ጉዳያቸው አልነበረም። ይህም ብዙ ሰራተኞችን ስራቸውን ላለማጣት ሲሉ ጤነኛ ያልሆነ ፉክክር ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸው ነበር።

በተደጋጋሚ ስራዬ በአመራሩ ብቻ ሳይሆን በስራ ባልደረቦቼም ጭምር በዝቅተኛነቱ ይገመገም ጀመር። አንድ በአመራር ውስጥ ያለች ሴት ስለ ቤተሰቤ ማወቅ ፈልጋ ዝም ብዬ ቀለል አድርጌ ነገርኳት። ከዛ ጓደኛዬ ሆና ነበር ግን ለካስ በማስመሰል ነበር። በኋላ ላይ ከኋላዬ እንደምታማኝ ደረስኩባት። የቢሮው መሳቂያ እንደሆንኩኝ ተሰማኝ እና በጣም እራሴን ወቀስኩኝ።

ጤናዬ ተቃወስ እና የደም ግፊቴ ከቁጥጥር ውጪ ሆነ

ጤናዬ ተቃወስ እና የደም ግፊቴ ከቁጥጥር ውጪ ሆነ። ብዙ ጊዜ በራስ የመተማመን ስሜቴ ዝቅተኛ በመሆኑ እና የማስታወስ ችሎታዬ ዝቅተኛ መሆኑ ያሰቃየኝ ነበር። ወዲያው ድብርት እና ጭንቀት ውስጥ ገብቼ እራሴን አገኘሁት። በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ከአልጋ ተነስቼ ስራ መሄድ አለብኝ። ወደ ቤት ስመጣ በጣም ደክሞኝ እና ተጨናንቄ በመሆኑ ከቤተሰቤም ጋር ያለኝ ግንኙነት እየሻከረ መጣ።

የምክር አገልግሎት በማግኘቴ ቤተሰቤ ሳይበተን ቀረ። ቤተሰቦቼም የስራዬ ሁኔታ ምን ያህል አስጨናቂ እንደሆነ ሲረዱልኝ ጤናዬም እየተስተካከለ መጣ። በጓደኞቼ እና በቤተሰቦቼ እርዳታ የመጨረሻውን አመት እንደምንም ተሻገርኩኝ። ከበጎ ፍቃደኞች ጋር መስራት ጀመርኩኝ። አዕምሮዬ መነቃቃት እና የተሻለ ትኩረት ማድረግ ጀመረ። የስራዬ ቦታዬ ያለው ውጥረት ግን አልቀነሰም። እንደውም እየተባባሰ ሄደ። ነገር ግን በእኔ ውስጥ የሆነ ነገር ተቀየረ። በምኖርበት አካባቢ በማህበራዊ ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ ሆንኩኝ። የሴቶች ማህበር ጠንካራ አባል ስሆን እና ሌሎች አባላቶች ለእኔ ያላቸውን አመለካከት ስመለከት መከበር የሚገባኝ መሆኔን አስተዋልኩኝ። በደንብ የማላውቃቸው ስዎች እንኳን ጥሩ አይደለም ብዬ የገመገምኩትን ስራዬን ጥሩ መሆኑን ይነግሩኛል። ምን ያህል እንደማበረታታቸው እና እኔን በማወቃቸው እድለኛ እንደሆኑ ይነግሩኝ ጀመር። ይህ ለእኔ ምትሀት ነው። በሚያስደነግጥ ሁኔታ የማህበሩ ፕሬዝደንት እንድሆን ተጠቆምኩኝ።

በስራዬ የመጨረሻው አመት አንድ የስራ ባልደረባዬ ለቤተሰቡ የሆነ ነገር ፕሪንት እንዳደርግለት ጠየቀኝ። ያም የሰራዬ ማብቂያ ሆነ። ለካስ ፕሪንት እንዳደርግ የጠየቀኝ የስራ ባልደረባዬ ከስራ ሊያስባርሩኝ ባደረጉት ምክክር መሰረት ነበር። የድርጅቱ ጠበቃ ለምን እንዳደረኩት ጠየቀችኝ እና ምን እንደተፈጠረ ወዲያው ማወቅዋ ግራ አጋባኝ። በጣም በመጨነቄ ታመምኩኝ እና የሚቀጥለውን ቀን ስራ መሄድ አልቻልኩም። የድርጅቱ ጠበቃ ለእኔ ተከራከረችለኝ ግን ይህ ድርጊታቸው ሁሉም ነገር እንዲበቃኝ አደረገ። ስራዬን እንደማልፈልገው ግልጬላቸው መልቀቂያ ጠየኩኝ።

እነዚህያን 12 ዓመታት አሁንም እንደ ጨለማ ወቅት እቆጥራቸዋለሁ እና ስራ ከለቀቅኩኝ በኋላ በህይወቴ ተመልሼ ወደዚያ ቢሮ አልሄድኩኝም። ስራ ካቆምኩ በኋላ በደንብ አረፍኩኝ፣ ተኛሁኝ እና በሂደት አዕምሮዬ እና ሰውነቴ ተፈወሰ። የአመራርነት ስራ እንድሰራ ተመርጬ በጣም አመርቂ ውጤት አስመዘገብኩኝ። ምስጋና ለሚያበረታቱኝ እና ከጎኔ ላሉ ሁሉ ይሁንና በራስ መተማመኔ ተመልሶ በጣም ጥሩ ጓደኞች አገኘሁ። ባለቤቴ እና እኔ በበጎ ፍቃደኞች ማህበር ገብተን አሁን ሁለታችንም ደስተኞች ነን።

ጠንካራ የሆንኩት አስቸጋሪ በሆነ የስራ ህይወት ውስጥ ስላሳለፍኩኝ ነው?

ጠንካራ የሆንኩት አስቸጋሪ በሆነ የስራ ህይወት ውስጥ ስላሳለፍኩኝ ነው? አይደለም። አብሬያቸው ለመሆን የምፈልጋቸውን ሰዎች በመምረጤ ነው። እንዴት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መሻገር እንደምችል እና አስቸጋሪ ሰዎችን እንዴት ትቼ መሄድ እንደምችል ተማርኩኝ። በዚህ ፋንታ መልካም እና ስለእኔ ከሚያስቡ የእኔን ግብ እና አመለካከት ከሚጋሩ ሰዎች ጋር ህብረት ማድረግ ጀመርኩኝ። በስራችሁ ቦታ ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ ታፍናችሁ ካላችሁ ከአንድ ሰው ጋር ስለ ሁኔታው ማውራት በጣም ይጠቅማችኋል። ከታች ያለውን ቅፅ በመሙላት በነፃ የሚሰጥ ሚስጢር ጠባቂ የሆነ የእኛን አማካሪ ታገኛላችሁ። ምክንያቱም በዚህ ውስጥ ብቻችሁን ማለፍ የለባችሁም።


ይህንን ብቻውን መጋፈጥ የለብዎትም ፡፡ ከአማካሪ ጋር ይነጋገሩ ፣ ሚስጥራዊ ነው ፡፡


እኛ ከእርስዎ ጋር መገናኘት እንድንችል እባክዎ ከዚህ በታች ያለውን ቅጽ ይሙሉ ፡፡ ካልተገለጸ በስተቀር ሁሉም መስኮች ያስፈልጋሉ ፡፡

የእርስዎ ፆታ:
የዕድሜ ክልል:

ተገቢውን አማካሪ እንዲመድብዎት የእርስዎ ፆታ እና ዕድሜ እንጠይቃለን። የአገልግሎት ውሎች & የግል መረጃ ደህንነት ፖሊሲ.

እነዚህ ጉዳዮች ለመቋቋም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ እራስዎን ወይም ሌሎችን ለመጉዳት እያሰቡ ከሆነ ፣ እባክዎን ይህንን ያንብቡ!