የሁኔታዎች ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ማምራት

ልጅ እያለሁ ዝዋዥዌ መጫወት በጣም እወድድ ነበር፡፡ ወደላይ ወጥቼ ልቤ ስቅል ብሎ ስወርድ ደግሞ ሰውነቴ ቅልል ብሎ የምወድቅ ሲመስለኝ ከዛ በፍጥነት ወደላይ ስወጣ እንደገና እየተንደረደርኩኝ ስወርድ የሚሰማኝ ስሜት በተጫወትኩት ቁጥር ጫወታውን እንድወድ የሚያደርገኝ ነው፡፡ ወዲያው ወደኩኝ የሚል ፍርሃት ወዲያው ደግሞ ደስታ ወዲያው የፍርሃት ጩኋት ወዲያው ደግሞ የደስታ ሳቅ…. ዝብርቅርቅ ያለ የማይገመት የሆነ መሆኑ ያስደስተኛል፡፡ እያደኩኝ ስመጣ ግን ይሄ ሁሉ ቀርቶ ወዴት እንደምሄድ እንዳውቅ የሚረዳኝ የተረጋጋ፣ ተገማች እና ግልፅ የሆነ መንገድ በመምረጥ የሚገጥሙኝን ያልተጠበቁ ነገሮች ቀድሜ በማወቅ መንቀሳቀስ ጀመርኩ፡፡

ያለፉት ጥቂት ሳምንታት ግን ምንም መረጋጋት የሌለበት ነበር የሆነብኝ፡፡ እራሴን በፍፁም መገመት በማይቻል አላስፈላጊ የስሜት ዥዋዥዌ ላይ ሆኜ ነው ያገኘሁት እና ‹‹ከዚህ ላይ መውረድ እፈልጋለሁ›› እያልኩኝ በዝምታ እጮህ ነበር፡፡ ምክንያቱም ልብ አንጠልጣይ ነገር አልወድም፡፡ ከስራ ወደቤት እየተመለስኩኝ ታክሲ ውስጥ ሆኜ አጠገቤ የተቀመጠው አንድ ግለሰብ በጣም ያስለው ነበር፡፡ ያለሟቋረጥ ደረቅ ሳል ይስላል፡፡ ጊዜው ኮሮና ቫይረስ ከቻይና አልፎ አለም አቀፍ ራስ ምታት እየሆነ የነበረበት ጊዜ ስለነበር አጠገቤ የነበረውን ሰው በንቃት እና በትኩረት እንድከታተለው አድርጎኛል፡፡ ስለዚህ ወደቤት እንደገባሁኝ በአግባቡ እጄን ታጥቤ ልብሴን ቀይሬ ከቤተሰቤ ጋር ተቀላቀልኩኝ። አየሩ በጣም ቀዝቃዛ እና ዝናባማ ስለነበር ስለ ጎሮሮዬ መሻከር እና ስለመከርከሩ ብዙም አላሳሰበኝም ነበር፡፡ ምን አልባት በአየሩ ሁኔታ እያሳበብኩኝ ነበር፡፡ ከአምስት ቀናት በኃላ ግን የሚታይብኝን የበሽታዎቹን ምልክቶች መካድ የማይቻል ነበር፡፡ በእርግጠኝነት ታምሜአለሁ፡፡ ከዛን ጊዜ በኃላ በኮሮና ቫይረስ ላይ የሚቀለዱ ቀልዶች ሆነ የሚሳቁ ሳቆች ለእኔ ቀላል አልነበሩም፡፡ አንዳንዴ የተለመደ የሳይነስ በሽታዬ የተነሳብኝ ይመስለኛል፡፡

ከጥቂት ቀናት በኃላ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ሆነን ወደ ኮቪድ 19 ነፃ የጥሪ ማዕከል ደውለን የሚታዩብኝን ምልክቶች ገለፅን ነገር ግን ምርመራ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ምልክቶች እንዳልታዩብኝ ገለፁልኝ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን አብረውኝ ከሚሰሩት አንዳንዶቹ ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ምልክቶችን ማሳየት ጀምረው ነበር፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በየቤታችን ለይቶ ማቆያ ውስጥ ተቀመጥን፡፡ ከእኔም ጋር ግኑኝነት የነበራቸው የስራ ባልደረቦቼ፣ ቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ ለ14 ቀን ተለይተው ተቀመጡ፡፡ የምወዳቸውን ሁሉ የበከልኩኝ ስለመሰለኝ ተስፋ ቆርጬ በጣም አለቀስኩኝ፡፡ከሁሉም የሚብሰው የኮቪድ 19 ምልክት የሆነውን የትንፋሽ ማጠር እና ከባድ ሳል ይታይብኝ ጀመር፡፡ ነገር ግን በዚህም አላበቃም፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ በዚህ ጭንቀት ከጎን ሰው በሚያስፈልግበት ወቅት እራስን ማግለል እና ለብቻ መሆን እንደመፍትሄ መቀመጡ ጭንቀቱን የበለጠ ያደርገዋል፡፡

እኔ ምልክቱ እየተባባሰብኝ በመምጣቱ ወደህክምና ጣቢያ ሄጄ ምርመራ ካደረጉልኝ በኃላ የኮሮና ቫይረስ ጥርጣሬ ስለነበራቸው ወደ መመርመሪያ ጣቢያው ወሰዱኝ፡፡ ምርመራው ሲደረግልኝ የነበረው ድባብ በጣም ነበር የሚያስፈራው፡፡ ለሰዓታት በመመርመሪያው ክፍል ውስጥ ለብቻዬ ከተቀመጥኩኝ በኃላ ምርመራውን አደረጉልኝ፡፡ ሀኪሞቹ ጭንብል ለብሰው ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ታፍነው የምርመራ ናሙና ሊወስዱ ሲጠጉኝ በጣም ነበር የፈራሁት፡፡ ምርመራ የተደረገልኝ ቢሆንም ውጤቱ ገና ስላልደረሰ በለይቶ ማቆያው በመቆየት እራሴን ማስታመም ነበረብኝ፡፡ በጣም አስጨናቂ ጊዜ ነው፡፡ ይኖርብኝ ይሁን የሚለው ጭንቀት ከሚሰማኝ ህመም በላይ ያስጨንቀኛል፡፡ ምርመራውን ካደረጉልኝ ከሁለት ቀን በኃላ ከምርመራው ክፍል ተደውሎልኝ በምርመራ መሳሪያዎች እጥረት ምክንያንያት የኔ ምርመራ ውጤት ሳይነበብ እንደቀረ ተነገረኝ፡፡ እንደገና ሌላ ልብ አንጠልጣይ ነገር… ልክ እንደልጅነት ዥዋዥዌ የመውደቅ ያህል ስሜት ተሰማኝ፡፡ ከዛም ከምርመራው ክፍል እንደገና ተደወለልኝ፡፡ በውጤቱም ቫይረሱ እንደሌለብኝ ተረጋገጠ፡፡ በጣም ግራ ተጋባሁ፣ ጥርጣሬ ሞላኝ እና ሁሉም ነገር አልገባኝም፡፡ ምን አይነት ሰሜት ማስተናገድ እንዳለብኝ አላወኩም፡፡ የመገላገል ስሜት እንዲሰማኝ ማድረግ የነበረበት ዜና ወደሌላ የተጠላለፈ ዥዋዥዌ ውስጥ ከተተኝ፡፡

ከሁለት ሳምንት የለይቶ ማቆያ ቆይታዬም በኃላ አሁንም ልክ ኮቪድ 19 እንዳለበት ሰው ለይቶ ማቆያ ውስጥ ነኝ እና ቀጥሎ ያለው ጉዞዬ ወዴት እንደሚሆን ግልፅ አይደለም፡፡ ቫይረሱ ሳይኖርብኝ እንደዚህ ከሆንኩኝ ቢገኝብኝ ምን ነበር የምሆነው? ከእኔ ጋር አብረው የነበሩት ታዲያ ምልክቶቹ እንዴት ሊታይባቸው ቻለ? ለምን ያህል ጊዜ ነው ለይቶ ማቆያ ውስጥ የምቆየው? በድጋሚ ህይወቴ ወደ ቀድሞው ህይወቴ ሊመለስ ይችላል? በተለይ የመጨረሻው ጥያቄዬ የብዙዎቻችን ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ ይህ ወረርሽኝ በሚቀጥለው ወር ወይም አመት በህይወታችን ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ማናችንም አናውቅም፡፡ ማወቅም የምንችል አይመስለኝም፡፡ እንደኔ ደግሞ ልብ አንጠልጣይ የሆነ ህይወት መኖር ለማንወድ በዚህ ወቅት ህይወታችንን መምራት ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው፡፡ እውነታው ደግሞ ይህ ለመገመት የሚከብድ ወረርሽኝ ቢያበቃ እንኳን በአለማችን ላይ ሌላ ወዴት እንዲወስደን የማይታወቅ ጉዳይ መከሰቱ አይቀርም፡፡
በዚህ ጉዳይ ደግሞ ለብቻዬ እንዳልሆንኩኝ ማወቄ በጣም ይረዳኛል፡፡ ይህንን ግራ መጋባቴን እና ወደፊት ምን እንዲፈጠር አለማቄ እንደሚያስጨንቀኝ ለቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ ማማከር መቻሌ በጣም ነበር የጠቀመኝ፡፡ እነሱ አጠገቤ ባይሆኑ ምን እንደምሆን አላውቅም። እንደዚህ አይነት ከበድ ያሉ ጉዳዮችን ለብቻዎት መጋፈጥ የለብዎትም፡፡ ከታች የሚገኘውን ፎርም ይሙሉና አንድ አማካሪ ያግኙ፡፡ ይህ አገልግሎት ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀና በነፃ የሚሰጥ ነው፡፡

አማካሪዎቻችን በጉዞዋችሁ ውስጥ በርህራሄ እና በአክብሮት ከእናንተ ጋር ለመጓዝ ፍቃደኞች ናቸው፡፡

ፎቶ በ: Gift Habeshaw

ይህንን ብቻውን መጋፈጥ የለብዎትም ፡፡ ከአማካሪ ጋር ይነጋገሩ ፣ ሚስጥራዊ ነው ፡፡


እኛ ከእርስዎ ጋር መገናኘት እንድንችል እባክዎ ከዚህ በታች ያለውን ቅጽ ይሙሉ ፡፡ ካልተገለጸ በስተቀር ሁሉም መስኮች ያስፈልጋሉ ፡፡

የእርስዎ ፆታ:
የዕድሜ ክልል:

ተገቢውን አማካሪ እንዲመድብዎት የእርስዎ ፆታ እና ዕድሜ እንጠይቃለን። የአገልግሎት ውሎች & የግል መረጃ ደህንነት ፖሊሲ.

እነዚህ ጉዳዮች ለመቋቋም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ እራስዎን ወይም ሌሎችን ለመጉዳት እያሰቡ ከሆነ ፣ እባክዎን ይህንን ያንብቡ!