ከሁለት ክህደቶች ጋር መጋፈጥ

ከፍቅር ጓደኛዬ የተለየሁ የ24 ዓመት ሴት ነኝ። ከእሱ ጋር ፍቅር ይዞኝ ለአንድ አመት በፍቅር አብረን ዘልቀናል። ልንለያይ የቻልነው ጓደኛዬ ከሁለት ወር በፊት ከእርሱ ጋር ወሲብ መፈፀምዋን ደውላ ነግራኝ ነው። በጣም ያናደደኝ ከትዳር በፊት ወሲባዊ ግንኙነት ላለማድረግ ቃል ተገባብተን ስለነበር ነው። አሁን በቀድሞ ፍቅረኛዬ መከዳቴ ብቻ ሳይሆን ከሁለተኛ ክፍል ጀምሮ ጓደኛዬ በሆነችው እና እህቴ በምላት ጓደኛዬ መከዳቴ እንቅልፍ ነስቶኛል። የቀድሞ ፍቅረኛዬን ይቅርታ ላደርግለት እንደምችል አላውቅም ግን መልሼ አብሬው እንደማልሆን አውቃለሁ። ስለሴት ጓደኛዬ ደግሞ አሁንም ድረስ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም። እንደእሷ የቀረበ ጎደኛ ኖሮኝ አያውቅም እና ብቸኝነቱን እንዴት እንደምወጣው አላውቅም። ይህንን ጊዜ እንዴት ማለፍ እንደምችል ትንሽ ምክር ብትሰጡኝ በጣም ደስ ይለኛል።

ውድ ሀና፡-

ስለፃፍሽልን እናመሰግናለን። ይህ ላንቺ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው። በፍቅር ጓደኛሽ ብቻ ሳይሆን ህይወትሽን ሙሉ በምታውቂያት ጓደኛሽ ጭምር እምነትሽን አጥተሻል። ይህ ሁለት ጊዜ በጩቤ እንደመወጋት ነው። በዚህ ጉዳይ ለብቻሽ እራስሽን ከምታስጨንቂ ምክር መፈለግሽ የብልህ ሰው ውሳኔ ነው። ይህም በአንቺ በኩል ያለውን ትልቅ ብስለት ያሳያል። ከሁለት ክህደት ጋር እየተጋፈጥሽ ስላለሽ ከእያንዳንዳቸው ጋር ያለሽን አማራጮች እንመልከት፡

የፍቅር ጓደኛሽን በሚመለከት፡

የወሰንሽው ውሳኔ ትክክለኛ ይመስለኛል። የወሲብ ግንኙነት ለማድረግ እስከ ጋብቻ መታገስ ትክክለኛ ዉሳኔ ነው። የፍቅር ጓደኛሽም ለዚህ ተገዢ ነበር ነገር ግን ቃሉን መጠበቅ አልቻለም። ይህንን ላንቺ መደበቁ ትክክለኛ ማንነቱን ያሳያል። ይህም እስከጋብቻ ለመታገስ የሰጠሽን ቃል እንዲሁም ለአንቺ ታማኝ ለመሆን የገባውን ቃሉ ሊጠብቅ የማይችል ሰው ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው።

ምን ማድረግ አለብኝ? ሁለት አማራጮች አሉሽ።

  1. ወደእሱ ተመልሰሽ መሄድ ትችያለሽ

ግን መልሶ እሱን ማመን በጣም ከባድ ይሆናል እንዲሁም አስቀድሞ ቃል የገባልሽን ይጠብቃል ብሎ ማመኑ አስቸጋሪ ነው። ይቅርታ ይጠይቅሽ አይጠይቅሽ የጠቀስሽው ነገር የለም። አብራችሁ መሆን ብትችሉ እንኳን ይህንን ነገር በአግባቡ ካልተነጋገራችሁ ግንኙነታችሁ በጥርጣሬ የተሞላ ይሆናል። ብዙ ጥንዶች መከዳዳቶችን አልፈው ይኖራሉ ነገር ግን ብዙ ጥረት፣ መሰጠት እና ጊዜ የሚፈልግ ጉዳይ ነው። ይህንን መንገድ ከመረጥሽ ከአንቺ ጋር የምክር አገልግሎት እንዲያገኝ ጠይቂው። ለምን በአንቺ ላይ መማገጥ እንደፈለገ እና ለምን አንቺ ከምታውቂው ሰው ጋር እንዳደረገ ትክክለኛውን ምላሽ እስከምታገኚ ከዚህ ነገር ማገገሙ በጣም ከባድ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ማወቅ ያለብሽ አንቺን ከመውደዱ የተነሳ ከሚሳሳልሽ፣ እምነትሽን ከሚያከብር፣ ለስሜትሽ ከሚጨነቅ እና ለአንቺ ታማኝ ከሆነ ሰው ጋር መሆን የሚገባሽ ልጅ ነሽ። አሁንም ክብር እንዳለሽ ማመን አለብሽ። በማይረባ መንገድ ማንም ሊያይሽ አይገባም። ምንም አይነት ለውጥ ሳያሳይ በግንኙነታችሁ ከቀጠልሽ ለበለጠ ራስ ምታት እና መከዳት እራስሽን እያዘጋጀሽ እንደሆነ እወቂ።

  1. ከእርሱ ጋር ያለሽን ግንኙነቶች ሁሉ በማቋረጥ የራስሽን ህይወት መቀጠል ትችያለሽ

ይህ አጋጣሚ ለአንቺ እስከመጨረሻው ታማኝ ላይሆን እንደሚችል ምልክት ነው ወይም ከጋብቻ በፊት ለሚደረግ ወሲብም ሆነ በጋብቻ ውስጥ ለሚያደርገው ማመንዘር ማሳያ ሊሆን ይችላል። በጋብቻም ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ጥንዶች ከወሲብ ሊቆጠቡ ይችላሉ። አንደኛው በስራ ምክንያት ወይም በቤተሰብ ጉዳይ ለረዥም ጊዜ ወደ ሌላ ቦታ ሊሄድ ይችላል። አንዳችሁ ሆስፒታል ገብቻሁ ለሳምንታት ወይም ለወራት እዛ ልትቆዩ ትችላላችሁ። እርግዝናን ለእናት እና ለልጅ ጤንነት አንዳንዴ ወሲብ ማድረግን ሊከለክል ይችላል። አሁን የወሲብ ፍላጎቱን መቆጣጠር ካልቻለ ይህ ቀይ መብራት ሊሆን ይችላል። ታላላቅ ትዳሮች የሚመሰረቱት በወሲብ ሳይሆን በመተማመን ነው።

የሴት ጓደኛሽን በሚመለከት፡

ምርጫዎችሽ ተመሳሳይ ናቸው። ጓደኛዋ ሆነሽ መቀጠል ትችያለሽ ግን ከዚህ በፊት ያልነበረ ያለመተማመን ስሜት እንደሚኖርሽ አትጠራጠሪ። ታማኝነትዋን ትጠራጠሪያለሽ እና ለምን ለአንድ ለሊት ደስታ ብላ የአመታትን የዘለቀ ጓደኝነታችሁን ማክበር እንዳልቻለች ትጠይቂያለሽ። በሌላ በኩል መጥታ የተፈጠረውን ነገር ስለነገረችሽ በዚህ ከእሱ ትሻላለች። ቁጭ ብላችሁ በአግባቡ ልትነጋገሩ ይገባል። አንቺ እና እሱ አብራችሁ መሆናችሁ እያወቀች ለምን ከእርሱ ጋር ልትተኛ ቻለች? ቅናት፣ ንዴት፣ በቀል ወይስ ፍቅር? የችግሩን ትክክለኛ ምክንያት መነጋገር አለባችሁ። አንቺስ? ለጋብቻ እሰከምትደርሺ የወሲብ ፍላጎት ፈታኝ ስለሆነ ግንኙነት ባትጀምሪ ይመረጣል። በዚህ ውስጥ ብቻሽን እንዳልሆንሽ አስቢ ብዙዎች በተለያየ ምክንያት ከጋብቻ በፊት ከሚደረግ ወሲብ እራሳቸውን አግልለው ይኖራሉ፤ ይህም ተገቢ ነው። የተለያዩ ምክንያቶች አሉ ለምሳሌ፡ ሀይማኖታዊ ክልከላዎች፣ የእርግዝና ፍራቻ፣ የበሽታ ፍራቻ ወይም ሌሎች ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

አንድ ግን በጣም ቢከብድሽም ማድረግ ያለብሽ ነገር አለ። ለፍቅር ጓደኛሽ እና ለሴት ጓደኛሽ ይቅርታ ማድረግ አለብሽ። ይህ ካልሆን አሁን የሚሰማሽ የጉዳት እና የንዴት ስሜት ለአንቺ መርዝ እየሆነ ይመጣል እና መላ ህይወትሽን አደጋ ውስጥ ይጥላል። ይቅርታ ማድረግ የማይችሉ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ውስጣቸውን የሚያጥሩ እና ማንም ወደ ልባቸው የማያስጠጉ ፈሪዎች ይሆናሉ። እነዚህ ስሜቶች አሁን እየተሰሙሽ ከሆነ ይህ የተለመደ ነው። ነገር ግን እንዲቆጣጠሩሽ አትፈቀጂላቸው። ይህ አንድ አጋጣሚ መጨረሻሽን እንዲወስን አትፍቀጂለት። ይቅርታ ማድረግ ከሚሰማሽ ህመም ነፃ ያወጣሻል ምክንያቱም ይህ የምርጫ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ይህ ጊዜ እና ጥረትን ይጠይቃል። ይህንን ለመልቀቅ እና ይቅርታ ለማድረግ ከወሰንሽ ከፊት ለፊትሽ በደስታ እና በፍቅር የተሞላ አስደናቂ ህይወት ይጠብቅሻል።

ነገር ግን ከሁለቱ ጋር ግንኙነትሽን መቀጠል አይጠበቅብሽም። ይቅርታ ማለት ልባችንን አጉል ቦታ ከሰበረ ሰው ጋር ግንኙነትን መቀጠል ማለት አይደለም። በእርግጥ የአንድን ሰው የባህሪይ ችግር ካስተዋልሽ በኋላ ልብሽን መጠበቅ እና ድጋሚ እንዳይጎዳሽ መስመር ማበጀት ተገቢ ነው። ይህንን ማድረግ እንድትችይ እንረዳሻለን።

በራስ መተማመንሽንና ማንነትሽን ገንቢ። በማንነትሽ መተማመን ይኑርሽ እና በእድገትሽ ውስጥ ያለውን አቅምሽን አስተውይ። አንቺ ልዩ እንደሆንሽ ለማወቅ የወንድ ጓደኛሽ ወይም የሴት ጓደኛሽ አያስፈልጉሽም። ዝቅ ያለ በራስ መተማመን በሆነ ሰው ለመወደድ ብቻ ደረጃሽን እና ዋጋ የምሰጪውን ነገር እንድታጪው ያደርግሻል። በእርግጥ ማድረግ የምትፈልጊውን ነገር እንዳታደርጊ ያደርግሻል። እውነተኛ እና ላንቺ የሚያስቡ እና ስላንቺ ስሜት የሚጠነቀቁ ጓደኞች ይገቡሻል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ሊረዱሽ የሚችሉ ሚስጥር ጠባቂ እና በነፃ የሚሰጡ አማካሪዎች አሉን። በዚህ ውስጥ እራስሽን ለመስራት ከተዘጋጀሽ በጣም ጠንካራ ትሆኛለሽ።


ይህንን ብቻውን መጋፈጥ የለብዎትም ፡፡ ከአማካሪ ጋር ይነጋገሩ ፣ ሚስጥራዊ ነው ፡፡


እኛ ከእርስዎ ጋር መገናኘት እንድንችል እባክዎ ከዚህ በታች ያለውን ቅጽ ይሙሉ ፡፡ ካልተገለጸ በስተቀር ሁሉም መስኮች ያስፈልጋሉ ፡፡

የእርስዎ ፆታ:
የዕድሜ ክልል:

ተገቢውን አማካሪ እንዲመድብዎት የእርስዎ ፆታ እና ዕድሜ እንጠይቃለን። የአገልግሎት ውሎች & የግል መረጃ ደህንነት ፖሊሲ.

እነዚህ ጉዳዮች ለመቋቋም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ እራስዎን ወይም ሌሎችን ለመጉዳት እያሰቡ ከሆነ ፣ እባክዎን ይህንን ያንብቡ!