በሞተ ትዳር መታሰር

በጋብቻዬ ውስጥ ለብቻዬ ነበርኩኝ። ባለቤቴ የእኔን ስሜት አይረዳም ደግሞም አያከብርም። ከሰባት አመት የእጮኝነት እና ከአስራ ሶስት አመት የጋብቻ ጊዜ በኃላ እንደማይተዋወቅ ሰው ሆነናል። አንዳችን አንዳችንን መረዳት ወደማንችልበት እና ግንኙነታችን ወደሻከረበት ደረጃ ደረሰናል።

እኔ እንዲሰማኝ እፈልጋለሁ፤ ስለእኔ ስሜት ግድ እንዲለው እና እኔ እያለፈኩበት ያለውን መንገድ እንዲረዳ እፈልጋለሁ። እርሱ ግን ይሄንን አይፈልግም። እንዴት ባሌ ብዬ ያገባሁት ሰው ከእኔ ይህን ያህል ሊርቅ ይችላል? ጠባዩ ነው እንዳልል ከእኔ ውጪ የሁሉም ሰው ምርጥ ጓደኛ ነው። ለሌሎች ሰዎች መካሪ፣ አማካሪ እና ምርጥ ጓደኛ ነው። እኔ ግን ሁሌም ሁለተኛ ምርጫው ነኝ። አይሰማኝም፤ አይረዳኝም። ሁልጊዜ የእኔም ጓደኛ መሆን ቢፈልግ ብዬ አስባለሁ። የሚሰማኝን ነገር ስነግረው ፈጥሬ የማወራ ስለሚመስለው ስለእኔ ስሜት ምንም ቦታ አይሰጥም። በአንድ ቤት እንደሚኖሩ ነገር ግን እንደማይተዋወቁ እና እንደማይነጋገሩ ሰዎች ሆነናል። አልፎ አልፎ እናወራለን ነገር ግን ካወራን በጭቅጭቅ ነበር የምንቋጨው። ሁሌ እንጨቃጨቃለን። ከእኔ አጠገብ መሆን ስለማይፈልግ በተለያየ ክፍልም እንተኛ ነበር።

ባለቤቴ ቤት ውስጥ ሲሆን ለእኔም ሆነ ለልጄ ሲል የሚያደርገው ምንም የለም። እርሱ በአካል አለ እንጂ ከተለየን አመታት ተቆጥረዋል። ግን ይህንን እውነት ውስጤ እንዲያምን አልፈልግም። አብዛኛውን ጊዜውን ከቤት ውጪ ስለሚያሳልፍ ልጄን ለብቻዬ ነበር ያሳደኳት። እርሱን ሰዎች በጣም ይወዱታል፤ ለሁሉም ጀግናቸው እሱ ነው፤ ሁሉንም ይሰማል፤ ይረዳቸዋል። ነገር ግን ለሁሉም መገኘቱ ከራሱ ቤተሰብ ነጥሎታል። እኛ ጋር የለም። ከገንዘብ እርዳታው ውጪ እንደቤተሰብ ያለን ግንኙነት ሞቷል።

ባለቤቴ የአልኮል እና የስራ ሱስ ነበረበት። ከእንቅልፉ እንደተነሳ መጠጣት ስለሚፈልግ ብዙ መጠጥ ቤት ውስጥ ያስቀምጣል። በብዛት ከስራ ቀን ውጪም ይሰራል። ማታ እንኳን መሽቶ ወደቤት እንዲመጣ ስጠብቀው እየሰራ ቢሮው ይቆያል ወይም ከጓደኞቹ ጋር ሲጠጣ ያመሻል። ወደቤት እንኳን ሲመጣ ከእኔ ጋር እንደመሆን መጠጡን ያለማቋረጥ መጠጣት ይጀምራል ወይም ሊነጋ ጥቂት እስኪቀረው ከስልኩ ጋር ተጣብቆ ስለሚቆይ ከእርሱ ጋር የማወራበትን ፋታ አላገኝም። ምግብ እንኳን አብረን የምንበላው በጣም ጥቂት ጊዜ ነው። በብዛት እራት በልቶ እንደሚመጣ በመግለፅ እንዳልጠብቀው ነግሮኝ ወደቤት የሚገባው ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ወይም ከዛም አምሽቶ ነው።

ሌላ ሴት በህይወቱ ውስጥ እንዳለች ሳውቅ በጣም ነበር የተረበሽኩት።

ሁሌም በስሜትም፣ በሃሳብም ሆነ በአካል ከእኔ ጋር ያለው ግንኙነት እንዳበቃ ይነግረኝ ነበር። ነገር ግን እኔ በጣም ስለምወደው የሚለኝ ነገር ከልቡ አይመስለኝም ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ሌላ ሴት በህይወቱ እንዳለች ያወቅኩ። በጣም ነበር የተረበሽኩት። ነገር ግን ሴሰኝነቱን ባውቅም እንዳላወቀ ዝም አልኩኝ። ስሜቱ እና አካሉ ከሌላ ሴት ጋር እንደሆነ ባውቅም ምንም እንዳልተፈጠረ እና እንዳላወቀ መኖር ጀመርኩኝ። እርሱን ማጣት ሰለማልፈልግ፤ ትቶኝ እንዳይሄድ ፈርቼ።

በመጨረሻም እየሆነ ያለው ነገር ግን ሲገባኝ መቁረጥ እንዳለብኝ ተሰማኝ። ከዚ በላይ ለእርሱ ልሰጠው የምችለው ነገር ስለሌለኝ ለብቻዬ መሆን ፈለኩኝ። እስከዛሬ በመታገሴ ከራሴ ጋር ተጣላሁኝ። ስለጉዳዩ ከእርሱ ጋር ካወራን እንጣላላን ከዛ ወደ መጠጡ ይገባል፤ ይህ እንዲሆን ደግሞ አልፈለኩም። ስለዚህ ከሌሎች ምክር ለማግኘት ወሰንኩኝ። ለድብርት የሚታዘዙ መድሀኒቶችንም መውሰድ ጀመርኩኝ። ይህም መዳን እስካልችል ድረስ የታመምኩኝ እና ብቸኛ እንደሆንኩኝ እንዲሰማኝ አደረገኝ።

እሱ በጣም በስራ የተወጠረ ስለሆነ ወይም አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው ሌላ ቦታ ስለሆነ በእኔ ህይወት እየተፈጠረ ያለውን ነገር አላስተዋለም። በሞተው በትዳራችን ውስጥ የራሱን ድርሻ መወጣት ስላልቻለ እኔ ቀስ በቀስ በውስጤ እየተሰባበርኩኝ እንደደረቀ ቅጠል እየረገፈኩኝ ነበር። እርሱ ስለሁሉም ነገር የሚወቅሰው እኔን ነው፤ ሁሉም ነገር የእኔ ጥፋት እንደሆነ ነው የሚያስበው። የሳይኮሎጂ አማካሪዎችን ለብቻዬ ማግኘቴን ስጀምር እሱ ለቤተሰቦቻችን እና ለጓደኞቻችን የአዕምሮ በሽታ ሰላለብኝ እንደሆነ ይነግራቸዋል።

ለአመታት እራሴ ላይ በር ዘግቼ ነበር።

ከነበረብኝ ከባድ ድብርት መላቀቅ የቻልኩት እራሴ እና እራሴ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ስጀምር ነው። ከቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ ውስጥ በማንነቴ የሚቀበሉኝን ሰዎች አገኘሁ። ጤናማ የሆኑ ህብረቶችን በመጀመሬ ጥፋት ከነበረው እና ከሞተው ጋብቻዬ አረንቋ ጎትቶ አወጣኝ። ወደ እግዚአብሔር ፊቴን በመመለስ ከእርሱ የተሰጠኝን የማያቋርጥ ፍቅር እና በእርሱ ዘንድ ያለኝን ተቀባይነት ተገነዘብኩኝ።

ለአመታት እራሴ ላይ በር ዘግቼ ነበር። የገጠመኝን ነገር ለማንም ባለማካፈሌ እና ለመታደስ ባለመፍቀዴ ያንን ሁሉ ጭንቀት ለብቻዬ መሸከም ነበረብኝ። የሞተውን ግንኙነቴ እንዲሞት ስተወው እንደገና እራሴን በማግኘት አዲስ መንገድ ጀመርኩኝ።

ለመዳን በጀመርኩት ችግሬን ለሌሎች የማካፈል መንገድ ይበልጥ ጤነኛ እየሆንኩኝ ነው። ያለፈኩበት መንገድ መሆን ከምችለው በላይ ጠንካራ አድርጎኛል። በተለያየ መልክ ህይወትን ኖሬለሁ፤ ጣፋጭም መራራም። ያሳለፍኩት ህይወት ዛሬ የሆንኩትን አድርጎኛል። አሁን ያለፈው የትግል ህይወቴ አላማ እንደነበረው አምኛለሁ።

ዛሬ ስሜቶት ተቀባይነትን እንዳጣ ከተሰማዎት ይህንን ስሜት ለብቻዎ መጋፈጥ የለቦትም። የማወራውን ሰው ማግኘቴ ለመዳን ባደረኩት ጉዞ ትልቅ ድርሻ አለው። አድራሻዎትን ከስር ካስቀመጡልን ከእኛ ቡድን ሚስጥር ጠባቂ የሆነ አንድ ሰው ሊረዳዎት ያገኞታል። ትክክለኛ ስሞትን መግለፅ ይችላሉ ወይም ሌላ።

Author's Name changed for privacy.
ፎቶ በ: Abel Gashaw

ይህንን ብቻውን መጋፈጥ የለብዎትም ፡፡ ከአማካሪ ጋር ይነጋገሩ ፣ ሚስጥራዊ ነው ፡፡


እኛ ከእርስዎ ጋር መገናኘት እንድንችል እባክዎ ከዚህ በታች ያለውን ቅጽ ይሙሉ ፡፡ ካልተገለጸ በስተቀር ሁሉም መስኮች ያስፈልጋሉ ፡፡

የእርስዎ ፆታ:
የዕድሜ ክልል:

ተገቢውን አማካሪ እንዲመድብዎት የእርስዎ ፆታ እና ዕድሜ እንጠይቃለን። የአገልግሎት ውሎች & የግል መረጃ ደህንነት ፖሊሲ.

እነዚህ ጉዳዮች ለመቋቋም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ እራስዎን ወይም ሌሎችን ለመጉዳት እያሰቡ ከሆነ ፣ እባክዎን ይህንን ያንብቡ!