የማይገመት ስቃይ

በቤት ውስጥ በሚደረግ ጥቃት ሊያደርስ የሚችለውን አካዊም ሆነ ስነልቦናዊ ጉዳት ካልደረሰብን በስተቀር መገመት የምንችለው አይደለም። በጣም ጥልቅ የሆነ እና አጥንትን ዘልቆ እስኪገባ ድረስ የሚያሳምም ነው። ጥቃቱ የሚደርስባችሁ በምታፈቅሩት ሰው ሲሆን ደግሞ ምድር ትገለበጥባችኋለች እና የሚያስደስታችሁ ነገር ሁሉ ወደ ባህር ልብ ይሰወራል። ህይወትም መኖርም ሁሉም በአንድ ጊዜ ትርጉም ያጣሉ። ስለዚህ የትኛውንም አይነት የቤት ውስጥ ጥቃት መታገስ አይገባም። ይህንን የተማርኩት በትዳሬ ነው። በደረሰብኝ ድብደባ የበለዘው ቆዳዬ ብቻ አልነበረም። ልቤ ቆሰለ፣ በጭንቅላቴም ውስጥ ትልቅ ጠባሳ አኖረ።

በመታኝ ቁጥር ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት ውስጥ እገባለሁ፤ እራሴን መቆጣጠር አልችልም። እንደዚህ ስሆን ደግሞ የበለጠ እኔን የሚጎዳበትን አቅም ያገኛል። እየተጣላን እያለ የእኔን ስሜት ለመረዳት ከሞከረ የሚወደኝ ስለሚመስለኝ ንዴቴን እረሳዋለሁ። ነገር ግን እንደዚህ የሚያሰቃየኝ የአልኮል ሱሰኛ ስለሆነ እና በጣም ጨካኝ ስለሆነ ነው። ልክ እንደ ባሪያው ነበር የሚረግጠኝ።

የአልኮል ሱሱ ከሚገባው በላይ ተጠናውቶታል። ሲጠጣ የማገናዘብ ችሎታውን ያጣል፤ ስሜቱን ይጎዳል በዚህ ጊዜ ነው በእኔ አካል ላይም አካዊም ሆነ ስነልቦናዊ ጥቃት የሚያደርሰው። ግራ የገባው ነገር ቢሆንም ምናልባት ከሚገባኝ በላይ እንደሚጎዳኝ የማስበው ከሚገባው በላይ ስለምወደው ነው ብዬ አስባለሁ።

ሴት ልጄ ሁል ጊዜ ‹እናቴ አንዳንዴ አባቴ አንቺን እንደሚመታሽ እኔንም ይመታኛል ብዬ እጨነቃለሁ› ትለኛለች፡፡”

የባለቤቴ እውነተኛ ማንነት ከቤተሰቦቼ እና ከጓደኞቼ በመደበቅ ለአመታት ያለምንም ምክንያት አፈቀርኩት። ነገር ግን ማንነቴን፣ ቅንነቴን እና ክብሬን በትዳሬ ውስጥ አጣሁት፤ ተናቅኩኝ ተስፋ ያጣሁ እና የተጣልኩኝ ሆንኩኝ። በሁሉም መንገድ በባለቤቴ የተጠላሁ ነኝ፤ የእኔ ነገር አይጥመውም። ያረጀሁ እና አገልግሎቱ በማብቃቱ ሊጥለው ካሰበው እቃ እንደ አንዱ ሆንኩኝ።

እርሱ በመታኝ ቁጥር በፊት ለእርሱ የነበረኝን ፍቅር እና አክብሮት ከስር መሰረቱ እየናደው እንደሆነ አልታወቀውም። በዚህ ወቅት አንድ ሰብዓዊ የሆነ ሰው ሚስቱን ከጠላ እንደሚያደርገው ቢፈታኝ ይሻለኝ ነበር። ግን ይህንን አያደርግም። ሰው ምን ይለኛል የሚለው በጣም ያስጨንቀዋል፤ ከእኔ ይልቅ የትም ለማያውቁት ሁሉ ይጨነቃል። ከእርሱ ጋር የቆየሁት ባፈቀርኩት ሰው ተስፋ መቁረጥ የለብኝም በሚል እና ያፈቀርኩት ሰው በዚህ ሰው ውስጥ የለም በሚል ሁለት ሀሳብ ተወጥሬ ስለነበረ ነው።

ያስደነገጠኝ ነገር ደግሞ ከእኔ ጋር በጋብቻ ተጣምረን ባለንበት ሰዓት ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት ጀምሮ ማግኘቴ ነው። ተጠራጥሬ ስጠይቀው ለአንድ አመት ያህል ዋሸኝ። ከዛ በፈለገ ሰዓት ይጠቀምብኛል በፈለገ ሰዓት ደግሞ ጥቃት ማድረሱን ቀጠለ። ውስጤ ተሰባበረ፤ እንደ እብድ ሆንኩኝ። ምግብም አልበላም አንቅልፍም አልነበረኝም። ከእርሱም ጋር ሆነ ከሌላ ሰው ጋር ምንም አላወራም ነበር። በሂደት የአዕምሮ ጭንቀት በሽተኛ ሆንኩኝ።

ይህ ሁሉ የሚሆነው በልጄ ፊት ነው። እኔም እርሱን የምታገሰው ለልጄ ስል ነበር። እርሷ አሁንም ድረስ ‹አባቴ እናቴን እንዴት እንደሚቀጣት ብታዩ፤ በመታጠቢያ ክፍል ይቆልፍባታል› ትላለች። ሁል ጊዜ ‹አባቴ አንቺን እንደሚመታሽ እኔንም ይመታኛል ብዬ እጨነቃለሁ› ትለኛለች።

ስለልጄ ብዬ ድብደባውን ታገስኩት። በጋብቻ ውስጥ የቆየሁት ልጄን ተፋተን ማደግ የለባትም በሚል ሀሳብ ነበር። ነገር ግን የእኛ ግንኙነት ለእርሷ ጤናማ እድገት በጣም አደገኛ ሆነብኝ።

መላው ማንነቴን አሳስሮ በያዘኝ በነዚያ አመታት ከእኔ ጋር መሆን እንደማይፈልግ እና እንድሞት እንደሚፈልግ ይነግረኛል። እርሱ ፊትለፊት እራሴን ለማጥፋት እስክወስን ድረስ ተስፋ ቢስ እንደሆንኩኝ እንዲሰማኝ ያደርገኛል። በዚህም ምክንያት አንድ ቀን ለጀርባ ህመም የተሰጠኝን መድሃኒት ሁሉንም በአንድ ጊዜ ዋጥኩት።

እራሴን ያገኙሁት በፅኑ ህሙማን ክፍል እራሴን ለማዳን ለአንዲት ትንፋሽ ስታግል ነበር። ህይወቴ የተዘበራረቀ የምኖርበትን ምክንያት አጣሁ። በቃ መሞት ብቻ ፈለኩኝ። ነገር ግን በዚህ ጊዜ ቤተስቦቼ አጠገቤ ሆነው ለአመታት ስፈልገው የነበረውን ድጋፍ ሰጡኝ። የሚያዳምጠኝን የሚያከብረኝን አገኘሁ። ከዚህ በፊት ከድብርት ማገገሚያ መድሀኒት ለግማሽ አመት ያህል ወስጃለሁ ግን አንዳቸውም አያውቁም። በሆስፒታሉ አልጋ ላይ ሆኜ ውድ የሆነቸውን ነፍሴን አካሌንም ሆነ ስነልቦናዬን ያለገደብ ስለሰባበረው ትዳሬ ስል ለማጥፋት በመሞከሬ አምላኬ ምህረት እንዲያደርግልኝ ጠየኩት። በልቤ ብዙ አለቀስኩኝ። ከሆስፒታሉ ስወጣ ስገባ እንደነበርኩት ደካማ ሰው አልነበርኩም።

አሁን የውስጥ ጥንካሬ ይሰማኛል፤ ያሳለፍኩት ስቃይ ምንም ነገር ሊበግረኝ እስካይችል ድረስ ጠንካራ አድርጎኛል። ተስፋ ከሌለው ግንኙነት ነፃ መውጣት እፈልጋለሁ፤ ለአመታት ከኖርኩበት የጭቆና ህይወት ነፃ መሆን አለብኝ። ገደለኝ እንጂ እልጠቀመኝም። ለራሴ ያለኝን ክብር እና በራስ መተማመኔን ገደለው እንጂ ምንም አልፈየደልኝም። እራሷን የቻለች በራስዋ የምትተማመን ሴት መሆን እፈልጋለሁ። በስተመጨረሻም በጥቃት በተሞላው ጋብቻዬ ተስፋ ቆረጥኩኝ። ከዚህ በኃላ ጥቃት እና መጠላትን መታገስ አልችልም። ምንም እንዳልሆንኩኝ እንዲሰማኝ ከሚያደርገኝ ሰው ጋር በአንድ ቤት መኖር ለማቆም ወሰንኩኝ።

በእኔ ላይ የነበረውን ሁሉንም ስልጣን ነፈኩት፡፡

እለት እለት የባሰ ጠንካራ ሆንኩኝ። ፀሎት እና ከሌሎች ሰዎች ያገኘሁት ምክር ከባዱን መንገድ አቀለሉልኝ። ሌላን ሰው ማማከር ግን እንዴት ያለ እረፍት ነው? እፎይ። ከልጄ ጋር ትርጉም ያለው ህይወት መኖር እንድችል አደረገኝ። በሂደት በእኔ ላይ የነበረውን ሁሉንም ስልጣን ነፈኩት። በስተመጨረሻም ያገባሁት ሊጠቀምብኝ እና ጥቃት ሊያደርስብኝ እንዳልሆነ ሲገባኝ ለልጄ በጥቃት የተሞላ ትዳርን ከማሳያት ለብቻዬ ባሳድጋት የተሻለ እንደሚሆን ወሰንኩኝ እና ተስፋ መቁረጤ ከእኔ ተለየኝ። እንደ ሲዖል ከነበረ ህይወት አዲስ ህይወት ለመጀመር በጣም ጠንካራ ሆኜ እያብለጨለጭኩኝ ወጣሁ። ሁሉም አለፈ፤ ተመስገን!

ከጥቃት ህይወት መውጣት ፈልጌ ነበር እና አደረኩት። በልቤ በማለቅስበት ጉዳይ ደግሜ ላላለቅስ ነፃ ወጣሁኝ። ዛሬ ከዛ አስከፊ እና በነውር ከተሞላ ህይወት መውጣት በመቻሌ ከልቤ እስቃለሁ። ተመትቼ ወድቄ ነበር ነገር ግን ተነሳሁ ጠንካራ እና ቆራጥ ሆኜ ተነሳሁ።

የትኛዋም ሴት አካላዊ ጥቃት ሊደርስባት አይገባም። ጥቃት ከደረሰባት ደግሞ ለብቻዋ አይደለችም። እርዳታ ለማግኝት እና አስፈላጊውን ውሳኔ ለመወሰን ዝግጁ መሆን አለባት። ከእኛ ቡድን አንድ ሰው ሊረዳዎት ይችላል። እባኮትን አድራሻዎትን ከስር ያስቀምጡልምን። እናገኞታለን።

Author's Name changed for privacy.
ፎቶ በ: Wongel Abebe

ይህንን ብቻውን መጋፈጥ የለብዎትም ፡፡ ከአማካሪ ጋር ይነጋገሩ ፣ ሚስጥራዊ ነው ፡፡


እኛ ከእርስዎ ጋር መገናኘት እንድንችል እባክዎ ከዚህ በታች ያለውን ቅጽ ይሙሉ ፡፡ ካልተገለጸ በስተቀር ሁሉም መስኮች ያስፈልጋሉ ፡፡

የእርስዎ ፆታ:
የዕድሜ ክልል:

ተገቢውን አማካሪ እንዲመድብዎት የእርስዎ ፆታ እና ዕድሜ እንጠይቃለን። የአገልግሎት ውሎች & የግል መረጃ ደህንነት ፖሊሲ.

እነዚህ ጉዳዮች ለመቋቋም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ እራስዎን ወይም ሌሎችን ለመጉዳት እያሰቡ ከሆነ ፣ እባክዎን ይህንን ያንብቡ!