በጎጂ መንገድ መኖር

የሶስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ የትምህርት ቤት ጓደኛዬን እኛ ቤት አብረን እንድናድር ጠየኩት። ቤተሰቦቹን ሲያሰፈቅድ ግን ‹እናትህና አባትህ ሰካራሞች ስለሆኑ እናንተ ቤት እንዳድር ወላጆቼ አልፈቀዱልኝም› አለኝ። በዛን ሰዓት ነበር ነገሮች የተገለጡልኝ። ለካስ ቤተሰቦቼ ጤነኛ ሰዎች አይደሉም። ወላጆቼ የአልኮል ሱሰኞች ናቸው።

ይህ ነገር ይበልጥ የተገለጠልኝ እኔ እና እህቴ ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር እራት ተጋብዘን ስንበላ ነበር። ቆይታው መጠጥም ሆነ ጭቅጭቅ አልነበረውም። ጨዋታ እየተጫወቱ ይበላሉ፤ ይዝናናሉ። ከእኛ ቤት የተሻለ መሆኑን ለመረዳት ጊዜ አልወሰደብኝም። ከዛን ጊዜ በኃላ በተቻለኝ አቅም ቤት ላለመሆን ጥረት ማድረግ ጀመርኩ።

አጎቴ እኛ ሰፈር ይኖር ስለነበር ወደ እሱ ቤት በመሄድ ከአባቴ እና ከእናቴ ስካር እና ጭቅጭቅ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን አመልጣለሁ። በሚቀጥለው ቀን ወደ ቤት ስመለስ እቃ ተሰባብሮ ቤቱ ተዘበራርቆ አገኛለሁ። በቃ ይህ የእኛ ቤተሰብ የሁል ቀን ታሪክ ነው።

የትኛውም ልጅ እኔ የሰማሁትን እየሰማ ወይም ያየሁትን እያየ ማደግ የለበትም።

አንዳንዴ ጭቅጭቁን ጥላቻ ትቼ ወደ መኝታ ክፍሌ ሸሽቼ እገባለሁ። ነገር ግን መኝታ ክፍሌ ምቹ መደበቂያ አይሆነኝም። ሲሰዳደቡ እና ሲደባደቡ ይሰማኛል። እኔ እያየሁ እና እየሰማሁ ያደኩትን ነገሮች የትኛውም ልጅ ሊያየው አይገባም። አባቴ እናቴን በኃይል ገፍትሯት የወገቧ አጥንት ተሰብሮ ሆስፒታል ተኝታ ታውቃለች። አባቴን ሳይሰክር አላውቀውም። አንዳንድ ቀን አባቴ ሰክሮ ይመጣና ከእንቅልፌ ቀስቅሶኝ የህይወቱን አሳዛኝ ክስተቶች እየነገረኝ ያለቅሳል፤ እኔ ልጅ ስለነበርኩኝ ዝም ብዬ እሰማዋለሁ። ለምንድነው የሚነግረኝ ብዬ ብዙ ጊዜ አስባለሁ።

የሆነ ጊዜ ላይ በህይወት የመኖሬን ትርጉም እስክጠራጠር ደርሼ ነበር። ከክፍሌ ፊትለፊት ያለውን ትልቅ ዛፍ እያየሁ እዚህ ላይ እራሴን ልስቀል እንዴ ብዬ ሁሉ ማሰብ ጀመርኩኝ።

በስተመጨረሻም ወደ ዩኒቨርስቲ በጥሩ ውጤት አለፍኩ እና ከዛ ቤት ልወጣ ቻልኩ። በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ ተግቼ ስለሰራሁ ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ቻልኩኝ። አባቴ ይህንን ሲሰማ በህይወቴ ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ በጣም እንዳኮራሁት ነገረኝ። አባቴን ስላስደሰትኩት በጣም ነበር ደስ ያለኝ።

እኔ አልኮል አልጠጣም ነገር ግን የአልኮል ተፅዕኖ ገፈት ቀማሽ ነኝ። ጤነኛ ያልሆነ ቤተሰብ ውስጥ በማደጌ ጤናማ ቤተሰብ ምን እንደሚመስል ማወቅ አቅቶኛል። ሚስት ካገባሁ እና አባት ከሆንኩ በኋላ እራሴን በማላውቀው ስሜት ውስጥ አገኘሁት።

ስሜቴን የመግለፅ ችግርም ነበረብኝ። ወላጆቼ ደስ የማይል ስሜትን ያለመጠጥ ሃይል ሲያስተናግዱ አይቼ አላውቅም። በተጨማሪ የራሳቸውንም ሆነ የልጆቻቸውን ስሜት ሲረዱም ሆነ ሲያዳምጡ አላስታውስም። እህቴ ወይም እኔ በሆነ ምክንያት ካለቀስን እንኳን አባቴ ‹አታልቅሱ ካልሆነ የምታለቅሱበትን በቂ ምክንያት እኔ እሰጣችኋለሁ› ይለናል፤ ያው ገርፌ አስለቅሳችኋለሁ ለማለት ነው። ዩኒቨርስቲ በነበርኩኝ ወቅት ወደ ቤት ለእረፍት መጥቼ ስመለስ ለስንብት እናቴን ሳቅፋት ዝም ብላ ነበር የቆመችው፤ መልሳ እንኳን አላቀፈችኝም። እሷ ፍቅሬን እንዴት እንደምትቀበል አታውቅም እኔ ደግሞ ፍቅር መስጠትን ገና እየተለማመድኩኝ ነበረ።

ለብዙ አመታት በብዙ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ኖሬአለው። ወደ ኃላ ተመልሼ አስብና በሌላ ቤተሰብ ውስጥ ማደግን እመኛለሁ። በዚህ አይነት ቤተሰብ ውስጥ ባላድግ ህይወት እንዴት የተለየች እንደምትሆን አስባለሁ። አባቴ ላይ ያለኝ ንዴት እና ምሬት በመብዛቱ በራሴም ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮብኛል።

ይቅርታ ማድረግን ካልተማርኩኝ ብስጭቴ መጥፎ ነገር ውስጥ እንደሚከተኝ አውቄለሁ።

በዩንቨርስቲ ጥቂት አመታትን እንዳሳለፍኩኝ የሆነ ሰው አባቴን ይቅር ማለት እንዳለብኝ ነገረኝ። ሁለት አማራጮች እንዳሉኝ ተረዳሁ። የመጀመሪያው ምርጫ ለእኔም ሆነ ለሚኖረኝ ግንኙነቶች ጥሩ ባይሆንም በምሬት፣ በንዴት እና ሁሉን ነገር በማጣት ስሜት ኑሮዬን መቀጠል ሲሆን ሌላው አማራጭ ደግሞ አስተዳደጌ ክፍተት እንዳለበት ተረድቼ እያረምኩኝ መኖር። ይቅርታ ማድረግን ካልተማርኩ ብስጭቴ መጥፎ ነገር ውስጥ እንደሚከተኝ አውቄለሁ።

ከዛ በኃላ አባቴን ያለምንም መስፈረት እንደምወደው ደጋግሜ እነግረው ጀመር። ይህም ከእርሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረኝ አደረገ። እርሱም ለእኔ ግልፅ ሆኖ ያወራኝ ጀመር። አንድ ቀን ለአባቴ አንድ ደብዳቤ ፃፍኩለት። ስለእርሱ የማስታውሳቸውን ጥሩ ነገሮች ብቻ መርጬ ፃፍኩለት እና ላኩለት። ለደብዳቤዬ ግን መልስ አልሰጠኝም። ለነገሩ ለደብዳቤዬ መልስ ሊፅፍ መቻሉንም እርግጠኛ አይደለሁም። ነገር ግን እናቴ እንዲህ ብላ መለሰችልኝ ‹አባትህ ደብዳቤውን አንብቦ አለቀሰ›። ይህ ለእኔ ትልቅ ቦታ የነበረው ክስተት ነበረ። አባቴ እስከሚሞትባት እለት ድረስ ከአባቴ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበረን።

የአልኮል ሱስ ያለባቸው ወላጆች አሉዎት? ያልተፈታ ችግር ተሸክመው እየተንቀሳቀሱ ነው? ለብቻዎትን አይደሉም። ከታች ያለውን ፎርም ከሞሉ ከእኛ ቡድን አንድ ሰው መልስ ይሰጦታል። ሚስጥሮት ይጠበቃል እንዲሁም በዚህ አገልግሎት የሚጠየቁት ክፍያ አይኖርም።

Author's initials used for privacy.
ፎቶ በ: Abel Gashaw

ይህንን ብቻውን መጋፈጥ የለብዎትም ፡፡ ከአማካሪ ጋር ይነጋገሩ ፣ ሚስጥራዊ ነው ፡፡


እኛ ከእርስዎ ጋር መገናኘት እንድንችል እባክዎ ከዚህ በታች ያለውን ቅጽ ይሙሉ ፡፡ ካልተገለጸ በስተቀር ሁሉም መስኮች ያስፈልጋሉ ፡፡

የእርስዎ ፆታ:
የዕድሜ ክልል:

ተገቢውን አማካሪ እንዲመድብዎት የእርስዎ ፆታ እና ዕድሜ እንጠይቃለን። የአገልግሎት ውሎች & የግል መረጃ ደህንነት ፖሊሲ.

እነዚህ ጉዳዮች ለመቋቋም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ እራስዎን ወይም ሌሎችን ለመጉዳት እያሰቡ ከሆነ ፣ እባክዎን ይህንን ያንብቡ!