ፈታኝ እውነታ
በህይወቴ ከሚደንቁኝ ነገሮች መካከል አንዱ የቤተሰቦቼ ትዳር ነበር። እርስ በእርስ ያላቸው መከባበር በጣም ሚገርም ነበር። በመካከላቸው አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ እንኳን ጉዳዩን የሚፈቱት ፍጹም በሰከነ እና በተረጋጋ መንገድ ነበር። ድምፃቸው እንኳን ለጎረቤት ለኔ ራሱ በቅጡ አይሰማም ነበር። እናም ቤተሰቦቼ ልክ በጋብቻ ቀናቸው ላይ እንደገቡት ቃል ከሞት በቀር ምንም እንደማይለያቸው እርግጠኛ ነበርኩ።
አባቴ ለትዳሩ ምን ያክል ታማኝና ትጉህ እንደነበረ እያየው ነበረ ያደኩት። ባል ማለት ምን መምሰል እንዳለበት፥ አባትነት እንዴት እንደሆነ ፤ ለትዳሬ ምን ያህል ሃላፊነት መውሰድ እና መወጣት እንዳለብኝ በደምብ እንዳስተማረኝ አምናለው። ለሚስቱ እና ለእናቴ ደግሞ የታመመችበትን ወቅት ጨምሮ በማንኛውም ሰአት ከአጠገቧ በመሆን ፍቅርንና ፅናትን በተግባር አሳይቶኛል። ይህንንም በጋብቻዬ ቀን ለአባቴ ምን ያህል አክብሮት እንዳለኝና የህይወቴ አርአያ እንደሆነ ነግሬው ነበር።
እናም ቤተሰቦቼ ልክ በጋብቻ ቀናቸው ላይ እንደገቡት ቃል ከሞት በቀር ምንም እንደማይለያቸው እርግጠኛ ነበርኩ።
እኔም አግብቼ ወልጄ የራሴን ቤተሰብ መምራት ከጀመርኩ 2 አመት ሆነኝ። በዚህ መሃል ግን በህይወቴ አስቤው የማላውቀው ነገር ተከሰተ። በቤተሰቦቼ መካከል አልፎ አልፎ ይከሰት የነበረው አለመግባባት እየከረረ መጥቶ አሁን ላይ የቀን ተቀን ክስተት መሆን ጀመረ። ይባስ ብሎ አለመግባባታቸው ከከረረ ቃላት መወራወር አልፎ ሆኖ በማያውቅ መልኩ እጅ ወደመሰነዛዘር አደገ። እነርሱ መሆናቸውን እስክጠራጠርና ማመን እስኪያቅተኝ ድረስ የማላውቃቸው ሰዎች ሆኑ። ትናንት የመልካም ትዳር ምሳሌ የሆኑት እና በብዙ ሰዎች ይወራላቸው የነበሩት ወላጆቼ ዛሬ ላይ ወደ ፍቺ ማቅናት ጀመሩ።
እንደልጅ መሃል ገብቼ ከመገላገል ባለፈ ሁለቱንም በግል በማነጋገር ችግሮቻቸውን ለመረዳትና በተረጋጋ መንፈስ በጋራ መነጋገር እንዲችሉ መጣር ጀመርኩ። ነገር ግን እንኳን ሙከራዬ ሊሳካ ቀርቶ ፤ ይልቁንም ሁለቱም ከእኔ ጋር አለመግባባት ውስጥ መግባት ጀመሩ። እንደውም በዚህ ሂደት ውስጥ ከሁለቱም በኩል እንደልጅ ስለ እነርሱ ብዙ መስማት የሌለብኝን ነገሮች በመስማቴ ለብዙ አመታት ተገንብቶ የነበረው አክብሮቴ ሲቀንስ ተሰማኝ። ዞሮ ዞሮ ጥረቴ መና ቀረ። ተለያዩ።
ትዳራቸው እንዲቀጥል ምን ማድረግ እችል ነበር? ማድረግ እየቻልኩ ያላደረኩት ነገር ምንድን ነው? የሁልጊዜ ጥያቄዬ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን በእናትና በአባቴ መፋታት ባዝንም ፤ መፋታታቸው ካልቀረ እንኳንም ካደኩኝና ከቤት ወጥቼ የራሴን ህይወት ከመሰረትኩኝ በኋላ ተፋቱ ብዬ አስባለው። በልጅነቴ ተፋተው ቢሆን ኖሮ እንዴት እሆን ነበር?
ብዙ ጊዜ በቤተሰቦቻቸው ውስጥ የፍቺ ታሪክ ያላቸው ልጆች፤ እነርሱም ትዳራቸውን የመፍታት እድላቸው ከፍተኛ ነው ሲባል ስለምሰማ በእጅጉ ውስጤን ይረብሸኛል። ከባለቤቴ ጋር የሚፈጠሩ ማንኛውም ትንንሽ ሊባሉ የሚችሉ አለመግባባቶች ሳይቀሩ ውስጤ ጭንቀት ይፈጥሩብኛል። ከዚህ ሃሳብ ለመውጣት ብዙ መጽሐፍትን ከማንበብ ባለፈ የተለያዩ ዘዴዎችን ለመጠቀም ብሞክርም ፤ ሊረዱኝ ግን አልቻሉም።
ወላጆቼ ከተፋቱ በኋላ ብዙ ነገሮች ተቀያይረዋል። በዓላትና የእረፍት ጊዜያት እንደበፊቱ በቤተሰብ የታጀቡ መሆናቸው ቢቀርም አማራጭ ስለሌለን በራሳችን መንገድ ማሳለፍን ተለማምደናል። ሁሌም ግን ፤ ምንም እንኳን እነርሱ በራሳቸው ምክንያቶች ባለመግባባት ሁለቱም ለመፋታት ቢወስኑም፤ ትዳራቸው እንዳይፈርስ ከሞከርኩት የበለጠ ምን ማድረግ እችል ነበር? ከሚል ሃሳብ ጋር እታገላለሁ።
በተመሳሳይ የህይወት መስመረ ውስጥ እያለፉ ከሆነ እና ታሪክዎን ሊያጋሩን ከፈለጉ ፤ እባክዎን ያነጋግሩን።
ይህንን ብቻውን መጋፈጥ የለብዎትም ፡፡ ከአማካሪ ጋር ይነጋገሩ ፣ ሚስጥራዊ ነው ፡፡
እኛ ከእርስዎ ጋር መገናኘት እንድንችል እባክዎ ከዚህ በታች ያለውን ቅጽ ይሙሉ ፡፡ ካልተገለጸ በስተቀር ሁሉም መስኮች ያስፈልጋሉ ፡፡
እነዚህ ጉዳዮች ለመቋቋም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ እራስዎን ወይም ሌሎችን ለመጉዳት እያሰቡ ከሆነ ፣ እባክዎን ይህንን ያንብቡ!