ለውድቀት የታዘዘ መድሃኒት

ከኮሌጅ እንደወጣሁ ማይግሬን (ከፍተኛ የራስ ምታት) ያመኝ ጀመረ። አስታውሳለሁ አንድ ከሰዓት በጣም አሞኝ ጠረጴዛዬ ላይ ተኝቼ ነበር ስለዚህ በእጄ ሙሉ የህመም ማስታገሻ ዋጥኩኝ እና ለሁለት ቀናት ተኛሁ። በሂደት ህመሙ ጠፋ። ግን ረዥም ጊዜ ሳይሆን - በየወሩ ከፍተኛ ራስ ምታቶቹ መመለስ ጀመሩ። ከጥቂት ወራት በኋላ ሀኪም ጋር ሄድኩኝ። ሞርፊን ወጋኝ እና የህመም ማስታገሻዎችን ሰጥቶኛል ወደ ቤት ላከኝ። ከሰዓቱን ሙሉ ከተኛሁ በኋላ ተነቃቃሁ። ስለዚህ በሚቀጥለውም ቀን መድሀኒቶቹን ወሰድኩ። አዕምሮዬ ውስጥ ያለ የማብሪያ ማጥፊያን እንደማጥፋት ነው፡፡ ክኒኖቹ ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ ያደርጋሉ እና ህመሙን ያጠፉልኛል። ሌላ ምን እፈልጋለሁ? በሚቀጥሉት አመት ወይም ሁለት አመት ውስጥ ራስ ምታት የሚጀምረኝ መስሎኝ ከተሰማኝ ማስታገሻዎቹን መውሰድ ጀመርኩ። ከዛ መተኛት ካልቻልኩ ወይም ስጨነቅ ወይም የማይመች ነገር ሲሰማኝ መዋጥ ጀመርኩ። ዞር ብዬ ሳየው ሱስ ውስጥ እየገባሁ እና ጥገኛ እየሆንኩ እንደሆነ እየገባኝ አልነበረም። አንድ አመት ካለፈ በኋላ ቀደም ብዬ መድሀኒቱን ላስሞላ ወደ መድሀኒት መደብር ስሄድ ፋርማሲስቱ ጠየቀኝ። በዛ ጊዜ ምርጫ ነበረኝ። ይሄንን እንደ ማስጠንቀቂያ እወስደዋለሁ? ወይስ በዚህ መንገድ እቀጥላለሁ። በሚያሳዝን ሁኔታ ትንሽ ለመቀለድ ሞከርኩ። ስለዚህ መድሀኒቱን ሰጠኝ። ከዛ ጊዜ ጀምሮ የቻልኩትን ያህል ኪኒን ለማግኘት ዘዴዎችን መፈለግ ጀመርኩ። ወደ ተለያዩ መድሀኒት ቤቶች እና ሀኪሞች ጋር ሄዳለሁ። ወደ ሁለት ወይም ሶስት የተለያዩ ሀኪሞች ጋር ሄጃለሁ እና መድሀኒቶችን ገዛለሁ። በሁሉም በኩል ጥሩ ልጅ ነበርኩ። ከክርስትያን ኮሌጅ ተመርቄያለሁ እና በልጅነቴ ነው ያገባሁት። ብዙ መድሃኒት የሰጠኝን ሀኪም በዛ ጊዜ ወደዋለሁ፤ ምክንያቱም ብዙ ኪኒኖችን ስለሰጠኝ፤ “እንግዲህ ሱሰኛ ማንነት የለብህም ስለዚህ ስለ እሱ አልጨነቅም።” ይለኝ ነበር፡፡

የሆነ ችግር እንዳለ አውቄያለሁ፤ ለሀኪሞች እና ለፋርማሲስቶች እና ለሚስቴ እየዋሸው እንደሆነ ሲገባኝ። ግን በዛው ልክ መድሀኒት ሳልወስድ ስቀር በጣም መጥፎ ስሜት ይሰማኛል። በጣም የሚያስጨንቅ የአካል እና የስሜት መዛባት ይሰማኛል ስለዚህ መድሀኒቴን መያዜ በጣም በጣም አስፈላጊ ሆነ።

ለሚቀጥሉት በርካታ አመታት መድሃኒቱን መውሰድ ቀጠልኩ፤ በየቀኑ ካልሆነ በየሁለት ቀኑ። መድሀኒቴ አልቆ የሚሞላበትን ቀን ሁሌ ቆጥራለሁ። በሂደት መድሃኒቶች የህይወቴ በጣም አስፈላጊ አካል እየሆኑ መጡ። መድሃኒቶቹ ሲያልቁብኝ ከስራ ቀርቼ ቤት ተኛለሁ። እና ከዛ የተወሰነ ካገኘሁ የድሮው ዳግም እሆናለሁ። ለራሴ ነግረዋለሁ “ያ የሚዋሸው እና ጊዜና ጉልበቱን መድሃኒት ለማግኘት በመፈለግ የሚያጠፋው - ያ በእውነት እኔ አይደለሁም። ሌላ ሰው ነው። ማድረግ ያለብኝን ነው እያደረኩ ያለሁት።”

የዛን ጊዜ ሱሰኛ ሆኜ ነበር። ግን በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው የጠየቁኙን። ሚስቴ ከስንት ጊዜ አንዴ ነው የምትጠይቀኝ ግን ህመም ውስጥም እንዳለሁ ታወቃለች። ምክንያቱም የክርስትያን ትምህርት ቤት አስተማሪ ነኝ እና አሰልጣኝ ነኝ እና የወጣቶች ፓስተር ነኝ፤ ማንም የእኔን መጥፎ ነገር ማሰብ አይፈልግም። ውሸቴን ለመስማት ፈቃደኞች ነበሩ።

የተወሰኑ አመታት በሱስ ውስጥ ከቆየሁ በኋላ፡ ትራማዶል ወደ ገበያው መጣ። ትራማዶል ከሱስ ነጻ ነው ተብሎ ነው የመጣው። ግን በድጋሜ በጣም ደስ የሚል ትልቅ ሀኪም ነበረኝ ብዙ ናሙና እጁ ላይ ነበረው። አንድ ቀን 50 ኪኒኖችን ሰጠኝ። በነፃ። በአመት ውስጥ ያለ ትራማዶል የምውልበት ቀን አልነበረም። በየስድስት ወሩ ውሸቶቼ ይጋለጣሉ። ሚስቴ ከተወሰኑ በላይ ኪኒኖችን መውሰድ እንደ ሌለብኝ ታውቃለች እና የታዘዘልኝን መጠን ብቻ እየወሰድኩ እንዳለሁ ነግራታለሁ። ግን ዘገየም ፈጠነም ከባንክ ሂሳባችን ብር ይጎድላል ወይም ሀኪም ቀጠሮዬን ለማረጋገጥ ቤት ይደውላል ወይም ፋርማሲስት ያዘዝኩት መድሀኒት እንደተዘጋጀ ሊነግረኝ ይደውላል። ይሄ ሲሆን አለቅሳለሁ እና እናዘዛለሁ እና በድጋሜ እንደማላደርገው እናገራለሁ። ለሳምንት ወይም ለሁለት ሳምንት ያለ መድሀኒት ሄዳለሁ እና ከዛ የሆነ ነገር ያስጨንቀኛል ስለዚህ ተጨማሪ አመጣለሁ። በዛ ወቅት እኔ እና ሚስቴ ወደ አዲስ አበባ ሄደን ትምህርቴን ለመቀጠል ወሰንን። በቀናት ውስጥ አዲስ ሀኪም አገኘሁ፤ ቦታ መቀየራችን መድሀኒቶቹን በቀላሉ እንዳገኝ አደረገኝ ምክንያቱ እንደ አዲስ ከሌሎች አዲስ ሰዎች ጋር መጀመር ችላለሁ። በዛ ላይ እንደ ጉዞ ወኪል ሽያጭ ሰራተኛ አዲስ ስራ አገኘሁ፥ አዲስ ሀኪሞች ያሉባቸውን አዳዲስ ክሊኒኮችን በየጊዜው እየሄድኩ ጎበኛለሁ። እሱ ግን ከስራ እንድባረር አደረገኝ፤ ብዙ ጊዜ የሽያጭ ስራዬን አልነበረም የምሰራው፤ በመንገዴ ያለ ሀኪም ጋር ሄጄ መድሀኒት ነበር የምወስደው።

ከዛ ሚስቴ በድጋሜ ያዘችኝ። ያወጣሁትን 700 ብር መመለስ ረስቼ፤ እንዳወጣሁም ረስቼ ነበር። ስለዚህ የዛኔ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ማገገሚያ ለመግባት የተስማማሁት። እውነት ለመናገር በጣም ነው የቀለለኝ። ይሄ ውሸት ከዚህ በላይ መደበቅ አልነበረብኝም። ሁሌም እርዳታ ማግኘት ፈልግ ነበር እና ማቆም ፈልግ ነበር፤ ግን በቂ አልነበረም። መጠቀም የሚያመጣቸውን ጉዳቶች መጋፈጥም አልፈልግም ነበር ግን መጠቀምም ፈልግ ነበር ምክንያቱም ደስ የሚል ስሜት እንዲሰማኝ ያደርግ ስለነበር፤ መንቀሳቀስ እንድችል ያደርግ ነበር። ግን ያን ቀን ሁሉንም ታሪክ አልነገርኳትም። ለተያዝኩበት ነገር ብቻ ነው ያመንኩት። ምን ያህል ሱሰኛ እንደሆንኩ ቀንሼ ነው የነገርኳት እና ምን ያህል እንደምታውቅ ማወቅ ስለፈለኩ ምን ያህል ውስጡ እንደገባሁ አልገለፅኩም። ሚስቴ እና እኔ ሁለታችንም አንዴ ወደ ማገገሚያ መሄድ ከጀመርኩ እስተካከላለሁ ብለን አስበን ነበር። መጀመሪያ ላይም ወደዚህ ነገር የከተተኝ አስተሳሰብ ይሄ ነበር፤ አሞሃል፥ ወደ ሀኪም ቤት መሄድ አለብህ፥ ያድኑሃል።

ማገገሚያ ውስጥ የነበርኩ ጊዜ ውሸቶቹ እና ሂሳቦቹ መቀነሳቸው ቀጠሉ። ለአመታት እንዳደረኩት ከሚስቴ የገንዘብ ሁኔታችንን መደበቅ አልፈለኩም። እና አንዴ ከወጣሁ በኋላ፤ እዳውን መጋፈጥ ነበረብኝ። ስለዚህ ያለውን ጭንቀት ለመጋፈጥ በድጋሜ መድሀኒቶቹን መጠቀም ጀመርኩኝ፤ በመጀመሪያ ትንሽ ነበር። ቀኑን ለማለፍ አንድ ብቻ ነው የምውጠው። ለራሴ የምነግረው ነው። ግን በስድስት ወር ውስጥ ማገገሚያ ከመግባቴ በፊት እወስድ የነበረውን የመድሀኒት መጠን መውሰድ ጀመርኩ፡ በቀን ከ20-30 ፍሬ ክኒን።

መጠቀም ስጀምር በጣም የሚያሳፍሩ ነገሮች ማድረግ ጀመርኩ። አንዴ አራት ህፃናት ልጆቼን ብቻቸውን ራሳቸውን ችለው እንዲውሉ ትቻቸው ወጣሁ። የወላጆቼን ስም ተጠቅሜ መድሀኒት ገዛሁ። የሰርግ ቀለበቴን ለአራጣ አበዳሪ አስያዝኩ። እፍረት ቢሰማኝም ባህሪዬን ለመቀየር በቂ አልነበረም። በህይወቴ ወሳኙ ነገር ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ ማድረግ ነበር። እና ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ ለማድረግ ደግሞ የማውቀው አንድ ነገር መድሀኒት መዋጥ ብቻ ነው። ስለዚህ ኡደቱ በድጋሜ ጀመረ። ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ እውጣለሁ እና ከዛ መድሀኒት ስራውን ሲያቆም፤ የባሰ መጥፎ ስሜት ይሰማኛል ምክንያቱም አሁን ጥፋተኝነት እና ሀፍረት ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ ይሄን ለማጥፋት ሌላ ክኒን ውጣለሁ፡፡ እና ዙረቱ መልሶ ይቀጥላል፡፡

ከሽያጭ ሰራተኝነቴ ከተባረርኩ በኋላ፤ ለቤተ-ክርስትያን የጉዞ አስተባባሪ በመሆን ስራ አገኘሁ፡፡ መስራት የምፈልገው ስራ ነበር፡፡ አንዴ ከተቀጠርኩ በኋላ የታሪኬን አንዳንድ ክፍል ነገርኳቸው ግን ትልቁን ችግሬ አልነገርኳቸውም፡፡ በጥንካሬ ነበር የጀመርኩት፡፡ መድሀኒት መዋጥ ቀነስኩ፡፡ ግን ብዙም ሳይቆይ ራሴን ለጭንቀት እና ለብቸኝነት ማጋለጥ ጀመርኩ፡፡ ጓደኞች ነበሩኝ ግን ማንም የሚያውቀኝ አልነበረም፤ ስለዚህ አሁንም መጠቀም ቀጠልኩ፡፡ “የሆነ ነገር ትክክል እንዳልሆነ ገባኝ፡፡ ለሀኪሞች እና ለፋርማሲሰቶች እና ለሚስቴ እየዋሸሁ ነበር፡፡ ግን ደግሞ መድሀኒት ያልዋጥኩ ቀን የሚሰማኝን መጥፎ ስሜት አውቃለሁ፡፡” ሶስት አመት እዛ ከሰራሁ በኋላ፤ ከግለሰቦች ላይ መግዛት ጀመርኩ፡፡ እና እጅ ከፍንጅ ተያዝኩ፡፡ በገሀድ ነበር ያሳፍራል፣ ያሸማቅቃል፣ ትልቅ ውድቀት ነው፡፡ ግን አሁን ምንም የሚደበቅ ነገር የለም፡፡ ሁሉም እውነታ ተጋለጠ፡፡ ስለዚህ ከስራ ተባረርኩ፡፡ ያ ጊዜ ነበር ሁሉም ነገር የተቀየረው፡፡ አስተዋይ ሆኛለሁ ብል ጥሩ ነበር እና በመጨረሻ ሁሉንም ነገር ተናዝዤ፤ ታሪኬን በሙሉ አካፈልኳቸው ብል ደስ ይለኝ ነበር፤ ግን ሌሎችን የእኔን ታሪክ ማካፍል ነበረባቸው እኔን ከዚህ ህይወት ለማውጣት፡፡ እና አሁን ያስከተለውን ውጤት መጋፈጥ ነበረብኝ፡፡ ትናንሽ ወንድ ልጆቼ ነበሩ ካምፑ ውስጥ እያደጉ ያሉ ሳይክል እየነዱ፤ ስዕል እየሳሉ እና ወደ መናፈሻ እየሄዱ፡፡ እና እያየኋቸው “አባታችሁ ከስራ ተባሯል በሱሱ ምክንያት” ብዬ መንገር አለብኝ፤ የአራት አመት ልጅ ይሄን መረዳት አይችልም! “ይቅርታ እና ከአሁን በኋላ አላደርገውም አትላቸውም!” ብለው ጠይቀውኝ ነበር። ሚስቴንም መጋፈጥ አለብኝ፡፡ “ሰላም አስታወሽ ሁሉም ነገር እንዴት ጥሩ እንደነበር? ከአሁን በኋላ አይደለም፡፡ አሁንም መድሀኒቱን እየተጠቀምኩ ስለሆነ ከስራ ተባርሬያለሁ፡፡” በጣም ተናዳ ነበር፤ ቢሆንም ግን ትታኝ የመሄድ ሃሳብ ኖሯት አያውቅም፡፡ ትሄዳለች ብዬ አስቤ ነበር እና ጥፋተኛ ናትም ብዬ አላስብም ነበር ብትሄድ፡፡

የምንሄድበት ቦታ ስላልነበረን፤ ለሌላ አንድ ወር እዛ እንድንቆይ ፈቀዱልን እና መዋጥ ስላቆምኩ የቤቱን እቃ ራሱ ማሸግ ማገዝ አቅቶኝ ነበር፡፡ እሱ ብቻ አይደለም የሚንከባከበኝ ሰው ያስፈልገኝ ነበር፡፡ ሰው ሳይጠብቀኝ የትም መሄድ አልችልም ነበር፡፡ ማንም አያምነኝም ነበር፡፡ አስታውሳለሁ፤ አምስት ደቂቃ ልጠብቅ እያልኩ ስውል፡፡ “አምስት ደቂቃ ልጠብቅ፡፡ አምስት ደቂቃው ሲያልቅ፤ መድሀኒት ለማግኘት መንገድ ፈልጋለሁ፡፡” እና ከዛ አምስት ደቂቃው ሲያልቅ፤ ሌላ አምስት ደቂቃ መቆየት እችላለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ይሄ ሁኔታ ለሁለት ሳምንታት ቀጠለ፡፡ አካላዊ ጥገኝነቴ በሂደት ቀነሰ እና በራሴ የተወሰነ መንቀሳቀስ ጀመርኩ፡፡ ስድስታችንም ከካምፑ ባለ ሁለት መኝታ ወደ ሆነ የወላጆቼ ኮንዶሚኒየም ገባን፡፡ ከስራ ከተባረርኩ በኋላ በተዓምር በወር ውስጥ ስራ አገኘሁ፤ አትራፊ ያልሆነ ሀገር በቀል ድርጅት ውስጥ፡፡ በሰዓት ወጥቼ በሰዓት ገባለሁ እና ያደርሱኛል እና ከስራ ይወስደኛል፡፡

የመጀመሪያው አመት ግማሹን እግሮቼ ይንቀጠቀጣሉ እና ያልበኛል ምክንያቱም ገና መድሀኒት አለመውሰዱን እየተለማመድኩ ስለሆነ፤ ትኩረት ማድረግ ይከብደኝ ነበር፡፡ እና ቢሆንም ነገሮች ጥሩ እየሄዱ ነበር፡፡ በየስድስት ወሩ እድገት አገኝ ነበር፡፡ ስራ ባቆምኩበት ጊዜ ዋና አስተዳዳሪ ነበርኩ፡፡ ካቆምኩ በኋላ የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ወራት፤ ህይወትን በድጋሜ ማጣጣም የምችል አልመሰለኝም ነበር፡፡ ቀለሞች ብዙ አይታዩኝም ነበር እና ነገሮች ስሜት አልነበራቸውም፡፡ ግን ከሁለት አመታት በኋላ፤ ቀስ በቀስ ተቀየሩ፤ በፊት ያዝናኑኝ የነበሩ በድጋሜ ያዝናኑኝ ጀመር፡፡ መድሀኒት የሚያምረኝ በጣም ቀነሰ ግን የማይመቸኝን ነገር ለማለፍ ያምረኛል፡፡ ግን ላለፉት ስምንት አመታት ነፃ ሆኛለሁ፡፡ እና በተዓምር ማይግሬኔ አይነሳም፡፡

የእኔ ታሪክ ከሌሎች ሱሰኞች በትንሹ ይለያል ምክንያቱም የቤተሰቤ እና የሚወዱኝ ሰዎች ድጋፍ ነበር፡፡ የመጨረሻ የወደኩ ጊዜ፤ ሁሉም ድልድዮቼም አልተቃጠሉም ነበር፡፡ ግን ወደ ኋላ ዞር ብዬ ሳየው ሁሉንም ነገር እና ሁሉንም ሰው ለማጣት ጥቂት እርምጃ ብቻ ነበር የቀረኝ፡፡ ድጋፍ የሚያስፈልግዎት ከሆነ፤ ከእኛ ቡድን መሀል አንድ ሰው ይሄን መንገድ አብሮት መሄድ ይፈልጋል፡፡ የትኛውም አይነት ሱስ ቢኖርቦት ብቻዎን አይደሉም፡፡ መረጃዎትን ከስር ይተዉልን እና ከእኛ ቡድን መሀል በቅርቡ አንድ ሰው ያናግሮታል፡፡


ይህንን ብቻውን መጋፈጥ የለብዎትም ፡፡ ከአማካሪ ጋር ይነጋገሩ ፣ ሚስጥራዊ ነው ፡፡


እኛ ከእርስዎ ጋር መገናኘት እንድንችል እባክዎ ከዚህ በታች ያለውን ቅጽ ይሙሉ ፡፡ ካልተገለጸ በስተቀር ሁሉም መስኮች ያስፈልጋሉ ፡፡

የእርስዎ ፆታ:
የዕድሜ ክልል:

ተገቢውን አማካሪ እንዲመድብዎት የእርስዎ ፆታ እና ዕድሜ እንጠይቃለን። የአገልግሎት ውሎች & የግል መረጃ ደህንነት ፖሊሲ.

እነዚህ ጉዳዮች ለመቋቋም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ እራስዎን ወይም ሌሎችን ለመጉዳት እያሰቡ ከሆነ ፣ እባክዎን ይህንን ያንብቡ!